
በኤንቢሲ ኢትዮጵያ «አጀንዳ» ፕሮግራም ላይ የቀረቡት የቀድሞ የአሰብ አስተዳደር ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አሊ ኢሳ አህመድ በሃገራችን ስላለው ወቅታዊ ጉዳይ እማኝ ከሆኑበት የአሰብ ታሪክ ጋር በማያያዝ ውይይት አድርገዋል::
ከኤርትራ መገንጠል በፊት የነበረችው አሰብ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው ነዋሪዋ ከመሃል ሀገር ሄዶ የሰፈረባት፣ የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ ሰራተኞችና የተለያዩ ነጋዴዎች በስፋት የሚንቀሳቀሱባት የንግድና የኢንዱስትሪ ማዕከል ነበረች። ነገር ግን የኤርትራን መገንጠል ተከትሎ የሻዕቢያ አገዛዝ በከተማዋ ላይ ባደረገው አጥፊ ፖለቲካ ምክንያት የኢትዮጵያውያን ንብረት ከጥቅም ውጪ እንዲሆን መደረጉን ያስታውሳሉ፡፡
በ1980ዎቹ መጨረሻ የተከሰቱት የፖለቲካ ውሳኔዎች ከተማዋን ወደ ታሪካዊ ውድመት መምራታቸውን እንዲሁም የኢትዮጵያውያን መኖሪያ ቤቶች ሆን ተብሎ እንዲፈርሱ መደረጋቸውን፣ ንብረቶች መወረሳቸውን እና የነጋዴዎች ሀብት በግፍ መነጠቁን ይገልጻሉ።

በወቅቱ የከተማዋ አስተዳደር ለቀይ ባህር አፋሮች የጋራ ንግድ ማህበራትን አቋቁሞ ገንዘብ ካሰባሰበም በኋላ ፍቃድ በመከልከል ንብረታቸውን እንደወረሰባቸው በማንሳት፣ ይህ አጥፊ አካሄድ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለስደትና ለችግር እንዳጋለጠ ያብራራሉ።
ዛሬ ላይ አብዛኛው ወጣት በመሰደዱ እና በከተማዋ የቀሩት አረጋውያን በመሆናቸው በማህበራዊ አገልግሎቶች እጥረት ምክንያት የሚሞቱ ሰዎችን ለመቅበር እንኳ አቅም ያለው የሰው ኃይል አለመኖሩን ያነሳሉ።
የቀይ ባህር አፋሮች ከኢትዮጵያና ከአውሳ ሱልጣኔት ጋር ያለው ታሪካዊና ባህላዊ ትስስር ሊበጠስ የማይችል መሆኑን ጠቅሰው፣ ጣሊያንም በቅኝ ግዛት ዘመኑ የአፋር ህዝብ በአውሳ ሱልጣኔት ስር መሆኑን አውቆና አክብሮ ይንቀሳቀስ እንደነበር በማስረጃ የተረጋገጠ መሆኑን አቶ አሊ ያብራራሉ።
በኤርትራ የሪፈረንደም ወቅት ለአፋር ህዝብ የመወሰን መብት እንዳልተሰጠውና ከ250 ሺ በላይ ህዝብ በሚኖርበት ነገር ግን ከ9 ሺ ያልበለጡት ብቻ ድምጽ መስጠታቸውን ሲያነሱ አብላጫው የህዝቡ አባል እንዳልተሳተፈ ያመላክታሉ።
አሁንም ቢሆን የቀይ ባህር አፋሮች በየአካባቢያቸው የጎሳ ግጭቶችና አለመግባባቶች ሲፈጠሩ መፍትሔ ፍለጋ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡና በሱልጣኑ ውሳኔ መሠረት እንደሚመሩም አቶ አሊ ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ። ይህም ህዝቡ በስነ-ልቦናውም ሆነ በታሪካዊ መዋቅሩ ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ቁርኝት ያልተቋረጠ መሆኑን ያረጋግጣል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የባህር በር ያጣችበት መንገድ ህገ-ወጥ እና በወቅቱ የነበሩ አካላት ታሪካዊ ስህተት ነው ያሉት አቶ አሊ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም የሚቆም እና መብቷን የሚያስጠብቅ አለመኖሩ ሀገሪቱን ለዚህ ኪሳራ ዳርጓታል ብለዋል። ኢትዮጵያ ያቀረበችው የባህር በር ጥያቄ ወቅታዊ፣ ሕጋዊና የሀገሪቱን ህልውና ለማስቀጠል የግድ የሚያስፈልግ መሆኑን ይገልጻሉ።
በ1983 እና 1987 ዓ.ም መካከል በነበረው የሽግግር ወቅት ሀገሪቱ ሕገ-መንግሥታዊ ከለላ ባላገኘችበት ሁኔታ የተወሰኑት ውሳኔዎች ተቀባይነት የሌላቸው መሆናቸው ያነሱት የቀድሞ የከተማዋ አስተዳደሪ ኢትዮጵያም እንደ ታላቅ ሀገር በሰጥቶ መቀበል መርህ ብቻ ሳይሆን፣ ታሪካዊና ሕጋዊ መብቶቿን መሠረት አድርጋ የባህር በር ጥያቄዋን ማስከበር እንዳለባት አጽንኦት ሠጥተው ይናገራሉ።
ሻዕቢያ ኢትዮጵያን ለማዳከም እና የባህር በር ጥያቄዋን ለማስቀየር ሲል ከሽብር አካላት ጋር በመቀናጀት፣ አለመረጋጋት ለመፍጠር ቢሞክርም፤ ይህ አካሄድ የሚሰራበት ጊዜ ማክተሙን በመግለጽ ኢትዮጵያ ታሪካዊና ሕጋዊ ሰነዶቿን አደራጅታ የባህር በር መብቷን በጽናት ማስከበር የሚያስችላት ጊዜ ላይ እንደምትገኝም አቶ አሊ ጠቁመዋል።
በ- የአብሥራ ተፈራ












