NBC Ethiopia
።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።
አንዳንድ ቀናት በታሪክ ውስጥ በቀን መቁጠሪያ ላይ ከተመዘገቡ ቁጥሮች በላይ ከባድና አሳዛኝ ትርጉም ይኖራቸዋል። በአንድ ሀገር የፖለቲካ አቅጣጫ፣ የሕዝቦች ግንኙነትና የደህንነት ሁኔታ ላይ የማይረሳ ጥቁር ጠባሳ የሚያሳርፉ ታሪካዊ ክስተቶች ይኖራሉ።
በኢትዮጵያ ታሪክም ከእነዚህ አሳዛኝ ክስተቶች መካከል ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. በሀገር አለኝታ በሆነው የሀገር መከላከያ ሰራዊት “ሰሜን ዕዝ” ላይ የተፈጸመው ድንገተኛና አስደንጋጭ ጥቃት በዋነኝነት ይጠቀሳል።
በዚያች ቀን ሌሊት በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል የተከሰተው ክስተት በአንድ ወታደራዊ ዕዝ ላይ በተፈጸመ ጥቃት ብቻ የተገደበ አይደለም። ለረጅም ዓመታት በፖለቲካና በሥልጣን ፍላጎት ሲንከባለል የቆየው ውጥረት፣ ሕወሓት በወሰደው እጅግ አደገኛና የፅንፈኝነት እርምጃ ወደ ከባድ ግጭት የተሸጋገረበት ወቅት ነበር።
የሰሜን ዕዝ ጥቃት በድንገት የተፈጠረ ክስተት ሳይሆን፣ ሕወሓት ያጣውን የስልጣን የበላይነት እና የህዝብ ቁቡልነት በኃይል ለመመለስ ያደረገው የእኩይ እንቅስቃሴው ውጤት ነበር። ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵያ የተጀመረው ሀገራዊ የለውጥ ሂደት በሕዝብ ዘንድ ትልቅ ተስፋን የፈጠረ ቢሆንም፣ የጥፋት ኃይሉ የሕዝቡን ውሳኔና ሕገ-መንግሥታዊ ለውጡን ከመቀበል ይልቅ ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር ግጭት ውስጥ መግባትን መረጠ።
በተለይም በ2012 ዓ.ም. በዓለም አቀፉ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የፌዴራል መንግሥት የዜጎችን ህይወት ለመታደግ ሲል አጠቃላይ ምርጫውን በሕገ-መንግሥታዊ አሰራር መሰረት ቢያራዝምም ፤ ሕወሓት በዕምቢተኝነት የመንግስትን ስልጣንና የሕግ የበላይነትን በመጣስ በትግራይ ክልል ሕገ-ወጥ ምርጫ አካሄደ።
ይህ እርምጃ ሀገሪቱን ወደ አለመረጋጋት ለማስገባት የሄደበት የተሳሳተ መንገድ ነበር። የጥፋት ኃይሉ ሰላማዊና ሕጋዊ የመፍትሔ መንገዶችን በሙሉ በመዝጋት ሀገሪቱን ወደ ግጭት አስገባት።
ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. እኩለ ሌሊት፣ የሕወሓት አመራር በታሪካችን ታይቶ የማይታወቅ እጅግ ዘግናኝና የክህደት ድርጊትን በ”ሰሜን ዕዝ” ላይ ፈጸመ። የትግራይን ህዝብና ሙሉ ሀገሪቱን ለብዙ አመታት ከማንኛውም ጥቃት ሲጠብቅ፣ ልማት ሲያለማና ከሕዝቡ ጋር ተጋብቶና ተዋልዶ ሲኖር የነበረውን የመከላከያ ሰራዊት ከጀርባው አጠቃው።
ጥቃቱ ከመጀመሩ በፊት በክልሉ የነበሩ የስልክ፣ የኢንተርኔትና የኤሌክትሪክ መስመሮች ሙሉ በሙሉ እንዲቋረጡ ተደረገ። የፅንፈኛዉ ልዩ ኃይልና ተባባሪ ሚሊሻዎች ሰራዊቱ በሰላም ተኝቶ በነበረበት ሰዓት ድንገተኛ ወረራ በመፈጸም የወታደራዊ ካምፖችንና ከባድ የጦር መሣሪያዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ሞከሩ።
የጥፋት ኃይሉ ለዘመናት የጠበቀውን ሰራዊት ከጀርባ ማጥቃቱ ፣ ሀገራዊ አለኝታ የሆነን ተቋም እንደ ጠላት በመቁጠር የተፈጸመ እውነተኛ “የእናት ጡት ነካሽነት” እና የፅንፈኝነት ጥግ ማሳያ ነበር።
በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመውን ጥቃትና የሀገር ማፍረስ ሙከራ ተከትሎ፣ የፌዴራሉ መንግሥት የሀገርን ሉዓላዊነትና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ለማስከበር ሲል ወታደራዊ የሕግ ማስከበር ዘመቻ አካሄደ።
ሕወሓት በመረጠው የኃይል መንገድ ምክንያት በተቀሰቀሰው በዚህ ጦርነት፣ በሀገሪቱ ላይ እጅግ ከባድ ሰብዓዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ውድመት ደርሷል። ብዙ ዜጎች ሕይወታቸውን አጡ፤ ሚሊዮኖች ተፈናቀሉ፤ በትግራይና በአጎራባች ክልሎች የሚገኙ መሰረተ ልማቶችም ወደሙ።
ፅንፈኛው ኃይል የስልጣን ፍላጎቱን ከሀገርና ከሕዝብ ሰላም በላይ በማስቀደም የተከተለው ይህ የተሳሳተ አካሄድ፣ በስተመጨረሻ በሕዝባችን ላይ የማይረሳ የታሪክ ጠባሳ ጥሎ አልፏል።
የጥቅምት 24ቱን ጥቃት ስናስታውስ፣ ሕወሓትንና መሰል ፅንፈኞችን በማውገዝ የሀገርን አንድነትና ሰላም ማስጠበቅ ሁልጊዜም ቢሆን የሁላችንም ሀገራዊ ኃላፊነት መሆኑን በመገንዘብ ሊሆን ይገባል።
በ-በረከት አስረስ
። ። ።
ማስፈንጠሪያውን (ሊንኩን) በመጫን NBC ኢትዮጵያን ይጎብኙ ይወዳጁ
https://linktr.ee/NBCEthiopiaTV
#NBCEthiopia
#ሆኖ_መገኘት
#Ethiopia












