ሆኖ መገኘት…

የተዘራ የጤፍ ቅንጣት ከሱ በጣም በብዙ እጥፍ የሚከብደውን አፈር ፈንቅሎ ይጐነቁላል፣የግድ ነው፤ ያለዚያ በስብሶ ይቀራል፡፡ አዲስ የተወለደ ጥጃ በተወለደበት ሰዓት ወይንም ደቂቃዎች በእግሩ ቆሞ ወደ እናቱ ጡት ይውተረተራል፣ አማራጭ የለውም፤ ያለዚያ ህይወት አይቀጥልም፡፡ መሆን አለመሆን ነው ምርጫው፡፡ ሰው መሆን ደግሞ ከዚህ በላይ ነው፡፡ ከደመ ነፍስ ያለፈ ነው፣ ሰው መሆን ከእንሰሳዊነት በላይ ነው፣ የስብዕና ልዕቀት፣ የማንነት ከፍታ፣ ዘላለማዊነት…. የሰው መሆን ደመነፍሶች ናቸው፡፡ ሁላችንም ውስጥ የምንመኘው ለማሳካት የምንፈልገውና መሆን የምንሻው ማንነት አለ፡፡ ሰው ከህልሙ ጋር ይፈጠራል፡፡ ለራዕዩ ይኖራል፡፡ መሆን ያለበት እና የሚፈልገውን ሆኖ መገኘት ግን ከህልምና ከምኞት በላይ ነው፡፡ ትጋት፣ ቁርጠኝነት፣ አንዳንዴም መስዋዕትነትን ይጠይቃል፡፡ ህብረተሰብ፣ ህዝብ ወይንም ሀገር የሚባለው አካል የግለሰብ ቅንጣቶች ስብስብ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር እያንዳንዳችን ህዝብ ወይንም ሀገር የሚባለው አካል ቅንጣት ክፍል ነን፡፡ ያለ ግለሰብ ወይንም ያለ ቅንጣቶቹ ስብስብ ህዝብም ሀገርም አይኖሩም፡፡ የየአንዳንዶች መሆን ወይንም ያለመሆን ውጤት ነው – ሀገርና ህዝብ፡፡

እንደ ማህበረሰብ ስለራሳችን የምንተርከው በርካታ መልካም ሃሳቦች፣ እሴቶች፣ ራዕዮች ይኖራሉ፡፡ የምንለው ወይንም የምንስለው ሀገር ወይንም ህዝብ ነባራዊ ሐቅ ይሆን ዘንድ የያንዳንዳችን የምንለውን ሆኖ መገኘት ወሳኝ ነው፡፡ ተግባርና ሃላፊነት በየአንዳንዱ እጅ ነው ያለው፡፡ ስኬት፣ ውጤት ወይንም የመኖር ግብና ዓላማ ልኬቱ ሌላ ምንም አይደለም፣ ሆኖ መገኘት ነው፡፡ ከተፈጥሮ፣ ከማህበራዊ እውነትና ከጊዜ ጋር ያለን ግንኙነት ለራሳችን ባለን ታማኝነትና ሀቀኝነት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ የመኖር ግባችን ነገን የተሻለ ለማድረግ፣ ዙሪያችንን ለሁሉም የሚስማማ የመኖሪያ አካባቢ ለማድረግ፣ ግንኙነታችንን የአዎንታዊ አስተዋጽኦ መስተጋብር ለማድረግ ያለመ የህይወት ግብ ሲኖረን ማለት ነው፡፡ የሰው ልጅ የሰውነት ደረጃውን የጠበቀ፣ ማንነቱን የተረዳና የመጠነ፣ ራዕዩን የለካ “እሱን” ይሆን ዘንድ “እሱ ራሱ” ወሳኝ ነው፡፡ እንደ ግለሰብ በህብረተሰብ ውስጥ ያለን ተግባርና ሃላፊነት የተለያየ ሊሆን ይችላል፡፡ ሁላችንም የቡድኑ ቅንጣት አካል ወይንም አባል መሆናችን እንደተጠበቀ ሆኖ ስምሪታችን ሊለያይ ይችላል፡፡ ዋናው ጉዳይ ሁሉም የሚጠበቅበትን ሆኖ መገኘት ነው፡፡

ቢቀሉንም ቢከብዱንም ልንመልሳቸው የሚገቡት ጥያቄዎች ተመሳሳይ ናቸው፡-

  • እያንዳንዳችን ሆነን ያለነው መሆን ያለብንን ነው ወይ?
  • ተግባራችንስ ምን ይላል?
  • በታማኝነታችን የተመሰከረልን፣ በአገልጋይነታችን የምንታወቅ፣ ለታይታ ግድ የሌለን፣ በውጤት የምናምን፣ ለመልካም ስራ የምንሽቀዳደም ከሚገባን በላይ የማንመኝና የማንወስድ፣ የሰው ሐቅ እንዳያልፍብን በእጅጉ የምንጠነቀቅ ግዴታችንን የምናስቀድም …..???

በያለንበት መሆን የሚገባንን ማወቅ ላይ ብዙ ችግር የለብንም፡፡ የሚጠበቅብንና የሚፈለግብንን የማወቅ ችግራችን ብዙ አይደለም፡፡ ምኞትና ህልም ላይም ያን ያህል እጥረት የለብንም፡፡  የጋራ ጉድለታችንና የጋራ እጥረታችን መሆን ያለብንን መሆን ላይ ነው – ሆኖ መገኘት !

VIDEOS

NBC Ethiopia Live Streaming

Welcome Back!

Login to your account below

Create New Account!

Fill the forms bellow to register

Retrieve your password

Please enter your username or email address to reset your password.

Add New Playlist

Are you sure want to unlock this post?
Unlock left : 0
Are you sure want to cancel subscription?