
በኤንቢሲ ኢትዮጵያ ጤና መርሐግብር ላይ ቃለ መጠይቅ ያደረጉት የአዕምሮ ህክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ዮሐንስ ባህረ ጥበብ ስለ ኤዲኤችዲ (ADHD) ወይም ትኩረት ስለማጣት ችግር ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ሀኪሙ እንደገለጹት የዚህ ችግር አይነቶች የተለያዩ ሲሆኑ፣ በአንዳንድ ሰዎች ላይ ትኩረት ማጣት ብቻ የሚታይባቸው አጋጣሚዎች እንዳሉም ጠቁመዋል።
የችግሩን ዋና ዋና ምልክቶች በተመለከተ ሲያስረዱም፣ በታካሚዎች ላይ ዋነኛ የሚባሉት የባህሪ መገለጫዎች ትኩረት ማጣት፣ መቅበጥበጥ እና ነገሮችን ሳያስተውሉ መወሰን መሆናቸውን አንስተዋል።
እነዚህ ችግሮች በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ የተለያዩ ማህበራዊ እና ስነ-ልቦናዊ ተፅዕኖዎችን ሊያስከትሉ እንደሚችሉም ተመላክቷል።በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ላይ የሚያደርሰው ተፅዕኖ ከፍተኛ በመሆኑ፣ የዚህ ችግር ተጋላጭ የሆነ ሰው ሊያከናውን ያቀዳቸውን ጉዳዮች እስከመርሳት ሊደርስ እንደሚችል ዶክተር ዮሐንስ ገልጸዋል።
V

በችግሩ የተጋለጡ ሰዎች የሚሰሩትን ስራዎች የማዘግየት እና ስራን ለነገ የማለት የተለመደ ባህሪ በችግሩ ተጠቂዎች ላይ በስፋት ይታያል ብለዋል። ለአብነትም ADHD ያለበት ሰው ለማጥናት ወይም በትኩረት ለመስራት እንደሚቸገር ሀኪሙ አብራርተዋል።
በዚህ ችግር የተጠቁ ግለሰቦች ከእቅድ ውጪ የሆኑ ግዢዎችን ሊፈጽሙ እንደሚችሉ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም የገንዘብ አጠቃቀም እና የውሳኔ አሰጣጥ ላይ ችግር እንደሚፈጥርባቸው ያሳያል።
በተጨማሪም የማያቋርጥ ጭንቀት ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉ እና እራሳቸውን ዝቅ አድርገው እንደሚመለከቱም ተናግርዋል።
የችግሩን ትክክለኛ የህክምና መረጃ ለማግኘት እና ለመለየት ክሊኒካል ቃለ መጠይቆች እንደሚደረጉ እና ከብዙ የተለያዩ ምንጮች መረጃ በማሰባሰብ ጥናት ማካሄድ እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።
ስለ መፍትሄው የተናገሩት ሀኪሙ ሰዎች ስራዎችን በሚያከናውኑበት ወቅት ተገቢውን እረፍት እየወሰዱ መሆን እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
በ ታደለ ገበየሁ












