NBC ETHIOPIA
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን በአዋጅ ቁጥር 1238/2013 በተሰጠዉ ስልጣንና ኃላፊነት መሰረት መገናኛ ብዙሃን ተግባራቶቻቸውን በሀገራችን ሕግ፣ በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ እና የሙያ ስነ ምግባር አክብረውና ጠብቀው ተግባራቸውን ማከናወናቸውን የይዘት ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ፣ ለመገናኛ ብዙኃን ፈቃድና ምዝገባ የምስክር ወረቀት መስጠት፣ የማደስና እንዲሁም ከዚህ በተቃራኒ በህገ ወጥ የይዘት ስርጭት ላይ ተሰማርተው ሲገኙ ማገድ እና መሰረዝ ይገኝበታል፡፡

ስለሆነም በሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ሴንተር ኃ.የተ.የግል ማህበር ስር በሚታተሙ ሪፖርተር አማርኛ፣ ዘ ሪፖርተር እግሊዝኛ እንዲሁም ኢትዮጵያን ሪፖርተር የዲጂታል ፕላትፎርም ላይ የሚሰራጩ ይዘቶች ላይ ከአንድ ዓመት በላይ በባለስልጣኑ በተደረገው የይዘት ክትትል ተደጋጋሚ የህግና የሙያ ስነ ምግባር ጥሰቶች በሚዲያው መፈጸሙ ተረጋግጧል፡፡

በዚህም መሰረት በሪፖርተር አማርኛ፣ በዘሪፖርተር እንግሊዝኛ ጋዜጣና የኦንላይን ስርጭት አስመልክቶ በባለስልጣኑ በተደረገው የይዘት ክትትል የሚከተሉት የህግና የሙያ ስነ ምግባር ጥሰቶች ተለይተዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል፡-
በተደጋጋሚ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ጋር የሚጻረሩ ይዘቶችን ማሰራጨት፣
በሀገር ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አውድ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ ያላቸውን ርዕሰ ጉዳዮች በማንሳት ከሚሰጣቸው አርዕስት/Headline/ ጀምሮ ማጮህ /Sensationalize/፣
በተለያዩ መድረኮችና ሪፖርቶች ላይ የሚገኙ ሀገራዊ መረጃዎችን አጠቃላይ አውዱን ተገንዝቦ መረጃን ከማድረስ ይልቅ በቁንጽል እይታ ላይ ተመስርቶ በመዘገብ በህብረተሰቡ ዘንድ ጥርጣሬና ብዥታን መፍጠር፣
የውጭ ኢንቨስትመንት፣ ቱሪዝምና ዲፕሎማሲ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚፈጥሩ የተዛቡ መረጃዎችን ማሰራጨት፣
የሀገር ገጽታን የሚያጠለሹ፣ የሀገርን ብሄራዊ ደህንነትን የሚጎዱ፣ የህዝቦችን አብሮነትና እሴት የሚሸረሽሩ መረጃዎች ማሰራጨት፣
ሚዛናዊነት የጎደለው አድሏዊ ዘገባዎችን ማሰራጨት፣
ከራስ ጥቅምና የግል ፍላጎት በመነሳት ባልተረጋገጠ መረጃ የተቋማትን ስምና ገጽታ ማጠልሸት፣
በመሆኑም ሪፖርተር ከላይ የተመለከቱት የህግና የሙያ ስነ ምግባር ጥሰቶችን እንዲያርም ላለፈው አንድ ዓመት ባለስልጣኑ በተደጋጋሚ ጊዜ ከሚዲያው ባለቤትና ዋና አዘጋጆች ጋር ባካሔደው ውይይት መታረም ያልቻለ በመሆኑ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ቢሰጠውም በሚያሰራጫቸው ይዘቶች ላይ መሻሻሎች ባለመታየታቸው በአዋጅ ቁጥር 1238/2013 መሰረት የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ሴንተር ኃ.የተ.የግል ማህበር (ሪፖርተር አማርኛ፣ ዘሪፖርተር እንግሊዝኛ ጋዜጣ እና የኦንላይን ስርጭቱ) የህግና የሙያ ስነ ምግባር ግዴታዎችን ተሟልተዉ ተግባራዊ እስኪደረጉ ድረስ የምዝገባ ምስክር ወረቀቱ ከሰኞ ጥቅምት 23/2019 ዓ/ም ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ ከህትመትና ከስርጭት ሙሉ በሙሉ ታግዶ እንዲቆይ የተወሰነ በመሆኑ ይሔው ተግባራዊ እንዲደረግ ባለስልጣኑ በጥብቅ ያሳስባል፡፡












