
የቀድሞው የፋኖ አመራር የነበሩት ማርእሸት ፀሀዩ በኤንቢሲ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጣቢያ “በጊዜ ግስ”መርሃ ግብር ላይ በነበራቸው ቆይታ የፋኖ አባላት ቅስማቸው መሰበሩን ገለፁ።
እንደ ማርእሸት ገለፃ ይህም የሆነው የትግራይ ሃይሎች በደረሰባቸው ከባድ ወታደራዊ ምት የተነሳ ወደ ኤርትራ መሸሻቸውን ተከትሎ፣ የተማመኑበት ፅምዶ በመፍረክረኩ ምክንያት ተስፋቸው ሙሉ በሙሉ መሟጠጡን አብራርተዋል ።
በቃለመጠይቁም ፋኖ ወደ መደበኛ ጦርነት የሚመጣበት ወታደራዊ አቅም እንደሌለው በመግለፅ ህብረተሰቡ መማረሩንና በህዝቡ ዘንድም ያላቸው ተቀባይነት እጅግ አሽቆልቁሎ እንደሚገኝ አሰረድተዋል።

በሃገሪቱ እየተከሰቱ ያሉትን አዳዲስ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችና የጸጥታ መዋቅር ለውጦች መሬት ላይ ባለው እውነታ በመነሳት ዝርዝር ምልከታቸውንም ሰንዝረዋል።
በፋኖ፣ በህወሃት እና በሻዕቢያ መካከል የተደረገው ህብረት መሠረት የሌለው እና የማይሆን ሃሳብ መሆኑን ገልጸዋል ። በሌላ በኩል “የህወሃት አመራሮችን ቸርቻሪ ናቸው” ያሉት አመራሩ ፣ ወጣቶችን ለከፋ ችግርና የጦርነት ሰለባ እየዳረጉ “በሰው ደም የሚነግዱ” መሆናቸውን አጋልጠዋል ።
አክለውም ህወሃት የትግራይን ህዝብ ሃብትና ንብረት ይዞ ወደ ኤርትራ እንደሚኮበልል፣ ሻዕቢያም ፋኖ እና ህወሀትን ለራሱ ጠባብ የፖለቲካ ጥቅም ብቻ እንደሚጠቀምባቸው ተናግረው እንደነበር አብራርተዋል ።
መንግስት ስራውን አላቆመም ያሉት ማርእሸት” ለዓመታት በጫካ ቆይተው በነበረበት ወቅት መንግስት በሙሉ አቅሙ እየተዋጋቸው ይመስላቸው እንደነበር፤ ነገር ግን የፌደራል መንግስት እየተጠቀመበት የነበረው አቅም እጅግ አነስተኛ መሆኑን መገንዘባቸውን ተናግረዋል።
የቀድሞው የፋኖ አመራር በመልዕክታቸው አሁን ላይ ከሚታዩት የውድመትና የችግር አዙሪቶች ለመውጣት ወደ ሰላም አማራጮች መምጣት ወሳኝ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተው፤ የኃይል አማራጭ ዘላቂ መፍትሄ እንደማያመጣ በመገንዘብ ሁሉም አካላት የሰላምን በር ማንኳኳት እንደሚገባቸው ጥሪ አቅርበዋል ።
በ- ታደለ ገበየሁ












