የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ አቶ ጌታቸው ረዳ “ኅብረት ወይስ ክህደት? ፀረ ኢትዮጵያ ጥምረት ከየት ወዴት” በሚል ርዕስ በተካሄደ የፖሊሲ ውይይት መድረክ ላይ ተገኝተው በሰጡት ሰፊ ማብራሪያ፣ “ጽምዶ” በመባል የሚታወቀው የዓማፂያን ጥምረት ሙሉ በሙሉ መፍረሱን ተናግረዋል ።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ኮሌጅ እና በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት አዘጋጅነት በተሰናዳው መድረክ ላይ ሚኒስትሩ እንዳብራሩት “ጽምዶ” የሚለው ቃል የትግርኛ ቃል ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ በኩል ያለው የትግራይ ሕዝብ በተለምዶ የሚጠቀምበት የፖለቲካ ቃል አይደለም። ይልቁንም ቃሉ ከኤርትራ የተጫነ “የባዕድ አስተሳሰብ” መሆኑን ጠቁመዋል። ይህ ጥምረት ለመመሥረት ረጅም ጊዜ ቢወስድበትም፣ በተግባር ግን አንድ ዓመት እንኳን ሳይሞላው በፍጥነት ፈርሷል ነው
የጥምረቱ ሃይሎች የተለያዩ የፖለቲካ ጥቅሞችና ዓላማዎች ስለነበሯቸው በጋራ መቀጠል አልቻሉም ያሉት አቶ ጌታቸው፣ ይህ ስብስብ በጊዜያዊ ጥቅም ላይ የተመሠረተ እንጂ የጋራ ራዕይ ያልነበረው በመሆኑ ለመፍረሱ ምክንያት እንደሆነም ገልጸዋል። በተጨማሪም በዓለም አቀፍ ደረጃ በቂ የዲፕሎማሲ ድጋፍ እንዳላገኘም አንስተዋል።
የኤርትራ መንግሥት የጥምረቱን ኃይሎች ወደ ወሎ አካባቢ እና አፋር እንዲገቡ እንዲሁም የጅቡቲን የንግድ መስመር እንዲቆርጡ፤ ሻዕቢያ ደግሞ ከጀርባ ሆኖ እንዲደግፍ በማድረግ መንግሥትን ለመጣል አቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ ይህ ስሌት ከመከላከያ ሠራዊት እውነተኛ ቁመና ጋር ፍጹም የማይጣጣም በመሆኑ ሳይሳካ እንደቀረ ጠቁመዋል።
በተለይ ህወሃት ከመቀሌ የወጣበትን ሁኔታ በተመለከተም፣ ውሳኔው የተላለፈው ገና መከላከያ ሠራዊት ኮረምና አላማጣን ከመያዙ በፊት በወቅቱ የነበረውን ወታደራዊና ስትራቴጂካዊ ሁኔታ በመገንዘብ እንደነበር ገልጸው፣ በተለይ በወሎ አካባቢ የነበረው የመከላከያ ሠራዊት ምት በጣም ጠንካራና ከፍተኛ በመሆኑ፣ አብዛኛው የጥምረቱ ኃይል በመመታቱ ምክንያት ከመቀሌ ለመውጣት መገደዳቸውን በዝርዝር አስረድተዋል።

የሻዕቢያ አገዛዝ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት እንዳይፈረም ከፍተኛ ርብርብ ማድረጉንና ፕሬዝዳንቱ “መጠረግ ያለበትን ኃይል ሳንጠርግ ፕሪቶሪያ ተፈረመ፤ ተደናቀፍን” በማለት ስምምነቱን በግልጽ መቃወማቸውንም ሚኒስትሩ አስታውሰዋል።
አቶ ጌታቸው በማጠቃለያቸው፣ የሻዕቢያ መንግሥት የዓማፂያንን አቅም አጋንኖ በመገመት የፈጸመው ስህተት አሁን ላይ ጥምረቱ በመፍረሱ ምክንያት ለራሱ ህልውና ከፍተኛ ስጋት ሆኖበታል። የሻዕቢያ አገዛዝ ጦርነቱን ከራሱ ድንበር አርቆ ኢትዮጵያን በማተራመስ ስትራቴጂካዊ ጥቅም ለማግኘት ሙከራ በመክሸፉ፣ ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ ላይ የሚያደዉንቅ ሴራ በአደባባይ ማቆም ወይም ከኢትዮጵያ ጋር መደበኛ ሰላም መፍጠር የሚሉ ሁለት ምርጫዎች ብቻ ከፊቱ እንደቀሩት አስገንዝበዋል።













