የአፍሪካ ዕጣ ፈንታ በጥቂት ሀገራት የሚወሰንበት ዘመን አብቅቷል ሲሉ ፕሬዝዳንት ፑቲን ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን (ዶ/ር) ጨምሮ ከ46 በላይ የአፍሪካ ሀገራት የተሳተፋበት 3ኛው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ በሞስኮ እየተካሄደ ይገኛል።
በጉባኤው የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ባደረጉት ንግግር፣ የአፍሪካ የወደፊት ዕጣ ፈንታ በጥቂት ኃያላን ሀገራት የሚወሰንበት ዘመን አብቅቷል ብለዋል።
አፍሪካን “የወደፊቱ አህጉር” ሲሉ የገለጹት ፕሬዝዳንቱ ፥ በፍጥነት እያደጉ ካሉ 20 ሀገራት መካከል 12ቱ በአፍሪካ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
አንዳንድ ሀገራት ማዕቀብና የኢኮኖሚ ጫናዎችን በመጠቀም አፍሪካን እንደገና ወደ ዕዳ ጥገኝነት ለመመለስ እየሞከሩ መሆኑን ያነሱ ሲሆን፣ አህጉሪቱ ሉዓላዊነቷን ለማስከበር አማራጭ የክፍያ ሥርዓቶችን መከተል እንዳለባት አስገንዝበዋል።
ሞስኮ ለዚህ ጉልበት የሚሆን ትብብር ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኗንም አረጋግጠዋል።
አፍሪካ የምግብ ሉዓላዊነቷን እንድታረጋግጥ በግብርናና መሰረተ ልማት ለመደገፍ ቁርጠኛ ነን ያሉት ፑቲን፣የቴክኖሎጂ ድጋፍን አጠናኮረን እንቀጥላለንም ብለዋል።
እንደ ብሪክስ ያሉ ጥምረቶች እየተጠናከሩ መምጣታቸው ለቀጣይ ትብብር ጉልበት የሚሰጥ እንደሆነም ገልጸዋል።
በ-ሰላማዊት ወንድወሰን
















