
የኤርትራን ነጻነት ለማወጅ የተሄደበት መንገድ ሁሉን ያሳተፈ እንዳልነበረና ህጋዊ ከለላ ሳይኖረው በኢህአዴግ የተፈጸመ ታሪካዊ ስህተት መሆኑን ከኤንቢሲ ኢትዮጵያ አጀንዳ መርሃ ግብር ጋር ቆይታ ያደረጉት የቀድሞ የአሰብ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አሊ ኢሳ አህመድ ገለፁ።
ኢትዮጵያ የባህር በር ያጣችው ህጋዊ ባልሆነ መንገድና በወቅቱ የነበሩ ሥርዓቶች በተለይም ኢህአዴግ በፈጸመው ስህተት ነው ሲሉ አቶ አሊ ተናግረዋል ።
የቀይ ባህር አፋር ህዝብ ከዚህ ቀደም በአሰብ ከተማ በንግድና በተለያዩ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ይታወቅ የነበረ ቢሆንም፤ የሻዕቢያ መንግስት ወደ ስልጣን ከመጣ ወዲህ ግን የአካባቢው ማህበረሰብ እንዲፈናቀልና እንዲሰደድ መደረጉንም ገልጸዋል።
አሁን ላይ አሰብ የቀደመ ልማቷ ጠፍቶ ለመኖሪያ እንኳ ምቹ እንዳልሆነች የጠቆሙት የቀድሞው ምክትል አስተዳዳሪ፤ የሻዕቢያ አገዛዝ ነጋዴዎችን በማሰርና ንብረታቸውን በመዝረፍ ህዝቡን ለስደት በመዳረጉ አብዛኛው የቀይ ባህር አፋር ህዝብ ወደ ኢትዮጵያ ፣ጅቡቲና የመን ለመሰደድ ተገደዋል ነው የሉት።

የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የህዝቡ የዘመናት ፍላጎት መሆኑን ያነሱት አቶ አሊ፤ ጥያቄውን ለማጣጣል የሚሞክሩ አካላት ታሪክንና ህግን የማያውቁ ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ እንደ ታላቅ ሀገር ህልውናዋን ለማስቀጠል፣ የራሷ የባህር በር ሊኖራት እንደሚገባ በመግለጽ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ይህንን ጥያቄ አደባባይ አውጥቶ በግልጽ ማቅረቡ ተገቢና ወቅታዊ እርምጃ መሆኑን አብራርተዋል።
በአሁኑ ወቅት በሻዕቢያና በህወሃት መካከል ተፈጠረ የተባለው ጥምረት ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን የቀድሞው ምክትል አስተዳዳሪ ገልጸው፣ ሻዕቢያ የኢትዮጵያን መንግስት ለማዳከም እና የሀገሪቱን የባህር በር ጥያቄ ለማደናቀፍ በማሰብ በትግራይ መሬት ላይ ውጊያ ለመቀስቀስ ቢሞክርም ያሰበው ሴራ ሳይሳካ ቀርቷል ብለዋል ።
አክለውም ከውጭ ሀይሎች የሚደረጉ ያልተገቡ ጫናዎች የሀገሪቱን ህጋዊ ጥያቄ ሊያስቀሩት እንደማይችሉ በመጠቆም፣ የኢትዮጵያ መንግስት መብቱን ለማስከበር በሰከነና ህጋዊ በሆነ መንገድ በቁርጠኝነት መስራት እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
በ ታደለ ገበየሁ












