። ። ። ። ። ። ። ። ። ። ።
አንጋፋና ታላቅ አርበኛ “የአፍሪካ የዲፕሎማሲ እናት” በመባል የሚታወቁት አምባሳደር ቆንጂት ሥነጊዮርጊስ ከ 50 ዓመታት በላይ ለኢትዮጰያ እና ለአፍሪካ ታላቅ ውለታን አበርክተዋል::
በ1940 ዓ.ም በሃረር ከተማ ተወልደው አድገዋል:: በጠንካራ እናታቸው በሚመራ ቤት ሲያድጉ የእናታቸው ቁጥጥር ባይለያቸውም ታላቅ ወንድማቸው በራሳቸው እንዲወስኑ የጣለባቸው ዕምነት ለደረሱበት ስኬ ጉልህ ሚና ነበረው::
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ወደ ለንደን በማቅናት የዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት በለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል::

አምባሳደሯ በለጋ እድሚያቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ለመቀላቀል በነበረው የሥርዓተ ፆታ ተፅዕኖ እልህ አስጨራሽ ፈተና ውስጥ በማለፍ ከዮዲት እምሩ በመቀጠል ሁለተኛዋ የኢትዮጵያ ሴት አምባሳደር ሆነዋል::
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ ልዑክ ጽሕፈት ቤት ውስጥ በቅኝ ግዛት ነፃነት ጉዳዮች ኦፊሰር በመሆን ያገለግሉ ሲሆን የአፍሪካ ሃገራት ከቅኝ ግዛት ነፃ እንዲወጡ በነበረው ዓለም አቀፍ ትግል ላይ የኢትዮጵያን ድምጽ በዲፕሎማሲያዊ መድረክ በማስተጋባት ከፍተኛ ሚና ተጫውተው ነበር::
ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጀምሮ እስከ አፍሪካ ህብረት ምስረታና የሽግግር ሂደት ድረስ የህብረቱ “የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል” በመሆን ሂደቱን በግንባር ቀደምነት በመምራት ሚናቸውን የተወጡ ሲሆን በኦታዋ (ካናዳ) ፣ ቪዬና (ኦስትሪያ) ፣ ካይሮ (ግብፅ) እና ቴልአቪቭ (እስራኤል) የኢትዮጵያ ባለ ሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል::

በምሥራቅ አፍሪካ ልማት በየነ መንግስታት ተቋም (ኢጋድ) መሪነት በነበረው የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት ሂደት ላይ ከሰኔ 2009 እስከ መስከረም 2011 ዓ.ም. ድረስ በልዩ አማካሪነት በብቃት ሃላፊነታቸውን ተወጥተው ።
“በሙያ ዘመኔ ለሃገሬ ባበረከትኩት አገልግሎት ኩራት ይሰማኛል፣ ያለምኩትን ሁሉ አሳክቻለው ብዬ አምናለሁ፣ ለዚህ ስኬት ሚስጥሩ ለስራዬ ያለኝ ከፍተኛ ፍቅር ነው” ያሉት አምባሳደርነበር ቆንጂት በኖሩበት ዘመን ቤተሰብ ሳያፈሩ ከሃገር ሃገር በመዘዋወር በትጋት ስራቸው ላይ ብቻ አተኩረው እንደኖሩ ይታወቃል::
አምባሳደር ቆንጂት በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ፣ በደርግ እና በኢህአዴግ በሶስት የተለያዩ የፖለቲካ ሥርዓቶች ውስጥ ሃገራዊ ጥቅምን በጽናት እና በጥንቃቄ በማስከበር ሰርተዋል::
ለአበረከቱትም የዕድሜ ዘመን አገልግሎት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ የተሰጠ የልዩ እውቅና እና የምስጋና ምስክር ወረቀት እንዲሁም የጃፓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የምስጋና ሽልማት ከብዙ ጥቂቶቹ ናቸው::
አንጋፋዋ ዲፕሎማት አምባሳደር ቆንጂት ሥነጊዮርጊስ በህክምና ሲረዱ ቆይተው መጋቢት 26 ቀን 2018 ዓ.ም በተወለዱ በ 86 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ይታወሳል::
በ-የአብስራ ተፈራ












