
በህዝብ ደምና በወጣቶች ላይ የሚነግዱ የትግራይ አማጺ ቡድኖች ወጣቱ ያለፍላጎቱ፣ ያለበቂ ስልጠና እና በሃሰተኛ ትርክት ከፍተኛ እልቂት ወዳለው የጦርነት መንገድ እየመሩት መሆኑን በኤንቢሲ ኢትዮጵያ “ጊዜ ግስ” ፕሮግራም ላይ ቆይታቸውን ያደረጉት የቀድሞ የህወሃት አባል ኮ/ል ገ/ዋህድ ኃይሉ ገልጸዋል::
በ2013 ዓ.ም. ጦርነቱ ሲቀሰቀስ የትግራይ ወጣት የመጀመሪያ አቋሙ ወደ ግጭት አለመግባት እና “በእኛ ምክንያት እንደገና ወደ ስልጣን ለመምጣት የሚደረግን ውጊያ አንቀበልም” የሚል እንደነበር ከኔ በላይ እማኝ የለም የሚሉት ኮሎኔሉ በወቅቱ ግጭቶች እየሰፉ በመምጣታቸው ወጣቱ ያለፍላጎቱ ወደ ውጊያው እንዲገባ መደረጉን ያብራራሉ።
በገጠር የሚኖረው አብዛኛው ሕዝብ እና ገበሬ የመገንጠል ፍላጎት ያልነበረው ቢሆንም ጦርነቱ እየቀጠለ ሲሄድ “ሀገረ ትግራይ” በሚል የተሳሳተ ፕሮፖጋንዳ ወጣቱ ተታሏል ነው ያሉት። አክለውም መሪዎቹንና ጀነራሎቹን ለትግራይ ዋጋ እንደሚከፍሉ ጀግኖች አድርጎ ያስብ የነበረዉ ወጣት አሁን እውነታውን ተረድቷል። የትግራይን ህዝብ እንደ ባርያ ንግድ ዘመን በስልጣን እና በእድሜ እየከፋፈለ ለግብፅ እና ለሱዳን በዶላር እየተሸጠ እነሱ ግን በቢሊዮን የሚቆጠር ሀብት ማከማቸታቸውንም ተናግረዋል።
የዚህ የሽብር ቡድን የጦር አበጋዞች ህዝቡን ሲያነሳሱ “አንድ ትውልድ ለመስዋዕትነት ይዘጋጅ” የሚል መመሪያ ሰጥተው ነበር ሆኖም ልጆቻቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ከጦርነቱ ርቀው በቅንጦት እንዲኖሩ ካደረጉ በኋላ በገጠር ያሉ የድሃ አባወራዎች ግን እስከ 6 ልጆቻቸውን በጦርነቱ ገብረዋል።

ኮ/ል ገ/ዋህድ እንደሚሉት፣ በምዕራብ እና በሌሎች ግንባሮች ወጣቱ ወደፊት .እንዲዋጋ ተደርጐ ወደ ኋላ እንዳይመለስ ደግሞ ከጀርባ የሚጠብቅ እና የሚገድል ራሱን “ፋኖ” ብሎ የሚጠራ ኃይል እንደነበረም ገልፀዋል።
በተጨማሪም በ2ዐ ቢሊዮን ዶላር የተገዙ ዘመናዊ መሣሪያዎች ወደ ክልሉ ቢገቡም መሳሪያዎቹን አገልግሎት ላይ ሳይውሉ በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ተማርከዋል ነው ያሉት።
ከተለያዩ አካባቢዎች ሕፃናትን ጨምሮ ወጣቶች በአፈሳ ተወስደው ወደ ውጊያ መግባታቸውን ያመላከቱት ኮሎኔሉ በቤንሻንጉል እና በአባይ አካባቢዎች የተማረኩ መኖራቸውን አንስተዋል። እነዚህ ለጦርነት ያልደረሱ ወጣቶች በየበረሃው አቅጣጫ ጠፍቶባቸው፣ መሪያቸው ማን እንደሆነ እንኳን ሳይረዱ መመለሻ አጥተው እስከ ደቡብ ሱዳን ድረስ መበታተናቸውን አስረድተዋል። ይህን አሳዛኝ ድርጊት ሲገልፁም “እሳት ላይ ተማግደዋል” ነው ያሉት።
በርካታ ወጣቶችን ጨርሷል በሚባለው ደርግ ሥርዓት ወቅት እንኳን የትግራይ ሕዝብና ወጣት በዚህ መልኩ ተሸጦና የዚህን ያህል እልቂት ደርሶበት እንደማያውቅ ታሪክ አጣቅሰዋል።
ኮሎኔል ገብረዋህድ በመልዕክታቸውም ኢትዮጵያ ላይ በኃይልና በጠመንጃ ሥልጣን የሚጨበጥበት ጊዜ ማክተሙን በመጠቆም የአማፂ ቡድኖች ከዚህ አጥፊ ጎዳና ወጥተው የሠላም አማራጭ እንዲቀበሉ ጥሪ አቅርበዋል።
አክለውም የትግራይ ሕዝብ የሀገርን ሉአላዊነትና ሰላም የሚነካ አላማ አንግቦ የሚመጣ ሀይል ቢኖር እንኳን “በቃ” በማለት የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ በጽናት ሊገፋበት እንደሚገባ አሳስበዋል።
መንግሥት በክልሉ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን በፍጥነት በመመለስ፣ ኋላ ቀር የሆነውን የክልሉን የፖለቲካ መንገድ በመቀየር የሕዝቡን የልማትና የሰላም ፍላጎት ሊያሳካ እንደሚገባም አፅንኦት ሰጥተዋል።
በ-የአብስራ ተፈራ












