NBC Ethiopia

ህገወጡ የህወሓት ቡድን ወታደራዊ አቅሙ ተዳክሟል ሲሉ በኤንቢሲ ኢትዮጵያ ግዜ ግስ ዝግጅት ላይ ቆይታ ያደረጉት ጀነራል ባጫ ደበሌ ተናገሩ ።
ከስድስት ዓመታት በፊት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ ላይ ተፈጽሞ የነበረው አሳፋሪ ጥቃት ሙሉ በሙሉ ተቀልብሶ፣ ሰራዊቱ ዛሬ በነበረበት የሀገሩ ዳር ድንበር ላይ እንደሚገኝ ጀነራሉ አስታወቁ።
የጥፋቱ ሀይል ስብስቦች ሁልጊዜም ለሰላም የማይሰሩ፣ ከጦርነት ውጪ ማሰብ የማይችሉ ፤ ስልጣንና ሀብት ብቻ የሚሹ ወንጀለኞች መሆናቸውንም አብራርተዋል።
በህዝብ ደም የተሰበሰበ እጅግ ከፍተኛ የገንዘብ መጠንና የተፈጸሙ ህገወጥ ድርጊቶች እንዳሉ በማስታወስ፣ እነዚህ አካላት ከህግ ተጠያቂነት እንደማያመልጡ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል ።
የትግራይ ህዝብ ለ50 ዓመታት ከተጫነበት የውንብድና አገዛዝ ነፃ መውጣቱን የገለጹት ጀነራሉ፣ የህወሃት ወታደራዊ ክንፍ በጥበብና በሃይል መደምሰሱን ጠቁመዋል።
ከዚህ በኋላ ዋናው ትኩረት ሊሆን የሚገባው በክልሉ ላይ ሰላምን ማረጋገጥ፣ ልማትና መልሶ ግንባታ ላይ መስራት እንደሆነም አሳስበዋል።

በአካባቢው የቀሩ ታጣቂዎች ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመለሱ የሚደረገው ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።
አክለውም የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አፅንቶ ለማቆየት የሚያስችል ጠንካራ መከላከያ ሰራዊት መፍጠር ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑንም ጀኔራሉ አንስተዋል። ከዚህ ባለፈም ለውጭ ሀይሎች የማይገዛ፣ ሀገሩንና ወገኑን የሚያስቀድም አዲስ የትውልድ ግንባታ ላይ ትኩረት ተደርጎ ሊሰራ ይገባል ብለዋል ።
ጥቅምት 24ን በየዓመቱ ማስታወስ ድርጊቱ እንዳይደገም ለማድረግና መስዋዕትነት የከፈሉትን ጀግኖች ሰራዊቶችን ለመዘከር እንደሚያስፈልግ በመግለፅ እንዲሁም የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በማንኛውም ጊዜ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት በአስተማማኝ ሁኔታ ማስከበር የሚችል ብቁ ሰራዊት መሆኑንም ጀነራሉ አረጋግጠዋል።
በ-ታደለ ገበየሁ












