
ኢራን እና አሜሪካ በኒውክሌር ዙርያ በመርህ ደረጃ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተገለጸ።
ኢራን እና አሜሪካ ለዓመታት የዘለቀውን የኒውክሌር ውዝግብ ለመፍታት በጄኔቫ ባደረጉት የሁለተኛ ዙር ቀጥተኛ ያልሆነ ድርድር በዋና ዋና መርሆዎች መግባባት ላይ መድረሳቸውን የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራቅቺ አስታውቀዋል።
በቀጣይ ለሚኖሩ ውይይቶች መነሻ የሚሆኑ መሪ መርሆዎች ላይ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ችለናል ሲሉም ነው ሚኒስትሩ ለመገናኛ ብዙሃን የተናገሩት።
የተደረሰው መግባባት ወደ ስምምነት ለመድረስ የሚደረገውን ጉዞ “መስመር ያስያዘ” ቢሆንም የመጨረሻ ስምምነት ላይ ለመድረስ ግን ገና ብዙ እንደሚቀረውና ሂደቱ ፈታኝ እንደሚሆን ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
ሁለቱም ወገኖች በሁለት ሳምንታት ውስጥ ዝርዝር የውሳኔ ሃሳቦችን ይዘው ለመመለስ ተስማምተዋል።
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣን እንደገለጹት ኢራን በሁለቱ ወገኖች መካከል ያሉ ልዩነቶችን የሚያጠብ “ዝርዝር የውሳኔ ሃሳብ” በሁለት ሳምንታት ውስጥ ለማቅረብ ቃል ገብታለች።
ዲፕሎማሲያዊ መሻሻል በመካከለኛው ምስራቅ ሊከሰት የሚችለውን የጦርነት ስጋት በመቀነሱ የዓለም የነዳጅ ዋጋ ከ1 በመቶ በላይ ቅናሽ አሳይቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢራን መንፈሳዊ መሪ አያቶላ አሊ ካሜኒ አሜሪካ በኢራን ላይ የምታደርገውን “የመንግሥት ለውጥ” የማምጣት ሙከራ እንደማይሳካ በትናንትናው ዕለት ባደረጉት ንግግር በድጋሚ አስታውቀዋል።
ዘገባው የሮይተርስ ነው
በሰላማዊት ወልደገሪማ












