February 21, 2026
“ቴሌስትሪም” የይዘት ፈጠራ አቅምን በማሳደግና ለሳተላይት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ በማስቀረት ለዲጂታል ኢትዮጵያ ሽግግር ገንቢ አበርክቶ እንደሚኖረው የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ ገለጹ፡፡ ኢትዮ-ቴሌኮም ደንበኞች የመረጃና የመዝናኛ ይዘቶችን መመልከት የሚያስችላቸውን ቴሌስትሪም (TeleStream) የዲጂታል አማራጭ አገልግሎት ይፋ አድርጓል፡፡

የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ቴሌስትሪም በመዝናኛ፣ ትምህርት፣ ጤና እና በተለያዩ ዘርፎች ይዘትን በማዘጋጀትና ለሚሊዮኖች ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል ነው፡፡ ቴሌስትሪም (TeleStream) የዲጂታል አማራጭ አገልግሎቱም ሃሳብ ያላቸው አካላት ይዘት በመፍጠር የሚያስተላልፉበት “ብሔራዊ የዲጂታል ይዘት መድረክ” መሆኑን አስታውቀዋል።

ኢትዮ-ቴሌኮም በየጊዜው የሁሉንም ዜጎች የዲጂታል ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ የቴክኖሎጂ አማራጮችን እያሰፋ እንደሚገኝ አንስተዋል። በዚህም በዲጂታል አማራጭ የቀረበው የቴሌስትሪም አገልግሎት ምስሎችን በ4k፣ 8k እና በHD ጥራት በማሳየት የሚያድግና የሚሰፋ የቴሌኮም አገልግሎት መሆኑን አብራርተዋል። የይዘት ፈጠራ ባለቤቶች ከመዝናኛ ባለፈ ለትምህርት፣ ጤና፣ ቱሪዝምና መሰል ትምህርታዊና ማስታወቂያ አገልግሎት የሚጠቀሙበት ዘመናዊ የዲጂታል መድረክ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሚዲያዎች፣ የፊልም አዘጋጆችና ሌሎች የይዘት ፈጠራ ተዋንያን ይዘት ላይ ብቻ ያተኩሩ፤ ለተደራሽነቱ ኢትዮ-ቴሌኮም ሃላፊነቱን ይወስዳል ብለዋል፡፡ ኢትዮ-ቴሌኮም ባለፉት ስድስት ዓመታት በቴሌኮም መሰረተ ልማት መስፋፋት ተጨባጭ ውጤት ማምጣቱን ገልጸዋል፡፡ በኢትዮጵያ 98 በመቶ መረጃ የሚተላለፈው በሳተላይት መሆኑን በመጥቀስ፤ የዲጂታል መረጃ ተጠቃሚዎች ሁለት በመቶ ብቻ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮ-ቴሌኮም በአሁኑ ወቅት ካሉት 87 ሚሊዮን ደንበኞች 50 ሚለዮን የሚሆኑት የብሮድባንድ ተጠቃሚ በመሆናቸው የቴሌስትሪም አገልግሎት ማግኘት ይችላሉ ብለዋል፡፡ የቴሌኮም መሰረተ ልማቶች አገልግሎት መስጠት የሚችሉበት ሽግግር እየተፈጠረ መሆኑን ገልጸው፤ 108 ሚሊዮን ደንበኞችን ማስተናገድ የሚያስችል አቅም ፈጥሯል ብለዋል። “ቴሌስትሪም” የይዘት ፈጠራ አቅምን በማሳደግና ለሳተላይት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ በማስቀረት ለዲጂታል ኢትዮጵያ ሽግግር ገንቢ አበርክቶ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

በዚህም ኢትዮጵያ ለሳተላይት ክፍያ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ ከማዳን ባለፈ ያልተቆራረጠ አገልግሎት መስጠት ያስችላል ብለዋል። ቴሌስትሪም አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን ይፈጥራል ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፤ የቴሌስትሪም ምርቶችን በዘመን ገበያ በማዘዝ በኢትዮ-ቴሌኮም የአገልግሎት ማዕከላት ማግኘት እንደሚቻል ገልጸዋል። የቴሌስትሪም ዲጂታል አማራጭ አገልግሎት ደንበኞችም የአገልግሎት ክፍያዎችን ባሉበት ቦታ በቴሌ ብር መፈጸም እንደሚችሉም አስረድተዋል።












