ትንፋሽ በሚሰልቡ፣ተመልካችን በስሜት ከሚያቁነጠንጡ የእግር ኳስ ጨዋታ ውስጥ ከህሊና የማይጠፉ በአስደናቂ ምትሃታቸውን የሚታወሱ ተጫዋቾች እልፍ ናቸው። እንደ ጥበበኛው ማራዶና እና ፔሌ፤ ወደዚህኛው ትውልድ ስንመጣ ደግሞ ሮናልዶ እና ሜሲን የመሳሰሉ ኮከቦችን ያስመለከተን ሜዳ እንደ አልሃጂ ዲዩፍ ያሉ ግራ ገብ ስብዕና ያላቸው በሜዳ ውስጥ ከሚያሳዩት ምትሃት ይልቅ ሜዳ ላይ በሚያሳዩት ነውጠኛ ባህሪ የሚታወቁ ተጫዋቾችም በርክተው ይገኛሉ።
የአውሮፓ እግር ኳስ ፍልሚያዎች በሌሉበት በዚሁ ወቅት የቀድሞ ተጫዋቾችን የት ደረሱ? በምን ሁኔታ ላይስ ይገኛሉ ስንል ለመጠየቅ ወደነናል። ዛሬ የምናስታወሰው ተጫዋች በበርካታ ክለቦች እየተጓዘ በመጫወት የሚታወቀውን፣ ከምንም በላይ በአወዛጋቢ ድርጊቶች የሚታወሰውን ኤል ሃጂ ዲዩፍን ልናስታውስ ወደናል።
ከብዙ እግር ኳስ አፍቃሪያን ትውስታ የማይጠፋው የ2002ቱ የኮሪያ-ጃፓን ዓለም ዋንጫ በርካታ ኮከቦች ለዓለም የተዋወቁበት መድረክ ሆኖ አልፏል። ብራዚል ሻምፒዮን በሆነችበት በዚያ ውድድር አፍሪካን ወክለው ከምድብ ጨዋታዎች አንስቶ ለተጋጣሚዎች ክስተት ከሆኑ ቡድኖች መካከል የአፍሪካዋ ሴኔጋል አንዷ ነበረች።
በዚያ የሴኔጋል ወርቃማ ትውልድ ፋዲጋ፣ ቡፓ ዲዮፕ እና ወጣቱ አጥቂ አል ሃጂ ዲዩፍ ነጥረው መታየት የቻሉ ኮከብ ተጫዋቾች ነበሩ። ከዓለም ዋንጫው ፍጻሜ በኋላ በበርካታ የአውሮፓ ክለቦች ዓይን ውስጥ የገቡት የሴኔጋል ኮከቦች ከቀድሞ ገዢያቸው ሃገር ፈረንሳይ የሚገኙ ክለቦች የብዙዎቹ መዳረሻ ለመሆን በቃ።
ነውጠኛው ኤል ሃጂ ኦሲናው ዲዩፍ አስቀድሞም በፈረንሳዩ ሬንስ አካዳሚ ይገኝ ስለነበር በዓለም ዋንጫው ባሳየው ብቃት መነሻነት ወደ ከፍተኛው ሊግ ተሳታፊው ሌንስ ለመዘዋወር አስቻለው። በልጅነት ዕድሜው ያሰለጠኑት አሰልጣኞች የሚሰጡት አስተያየት ተጫዋቹ ከመጠን ያለፈ እልሕኝነት እና ተጋፋጭነት ይታይበት እንደነበር ይናገራሉ። እልህኝነቱ ከአጥቂነቱ ጋር ተዳምሮ በሜዳ ውስጥ የሚኖረው ውጤታማነት ይረዳዋል በሚል በየዋህነት ቢያስቡም እንደተመኙለት አልሆነም።
በሌንስ የሁለት ዓመት ቆይታው 18 ግቦችን በማስቆጠሩ ከጆርጅ ዊሃ በኋላ በፈረንሳይ ሊግ የታየ ተስፋ የሚጣልበት ተጫዋች ተብሏል። በሊቨርፑል አምስት ዋንጫ በአንድ ዓመት በማሳካት የሚታወሱት ፈረንሳዊው አሰልጣኝ ጄራርድ ሁሊየር በ2002 የክረምት ገበያ አጥቂ በአንገብጋቢ ሁኔታ የሚፈልጉበት ጊዜ ነበር።
የዩሮፓ ሊግ፣ ኤፍ ኤ ካፕ፣ ካርሊንግ ካፕና የአሸነፊዎች አሸነፊን በማሳካት ያነቃቁ ቡድናቸውን በማጠናከር የጊዜውን ሃያላን ማንችስተር ዩናይትድ እና አርሰናልን የሚፎካከር ቡድን ለመገንባት ወሰኑ።
ሊቨርፒል የመጀመሪያ ምርጫ ያደረገውን ዲዩፍን 12 ሚሊዮን ፓውምድ ወጪ በማድረግ አስፈረመ። ሟቹ አሰልጣኝ ጄራርድ ሁዬ ተጫዋች ሲያስፈርሙ በሜዳ ላይ በሚያሳየው ብቃት ብቻ ሳይሆን ከሜዳ ውጭ ያለውንም ጠባይ በሚገባ በመፈተሽ ይታወቃሉ። እስከዛሬም ድረስ ለብዙዎች እንቆቅልሽ የሆነው ግን እንዴት ዲዩፍን አላጠኑትም የሚለው ጥያቄ ነው።
ዲዩፍ በፈረንሳይ ሊግ ተጫዋችነቱ የሚታወሰው የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾችን በመደብደብ፣ የቡድን አጋሮቹን አፍንጫ በመስበር እና ዳኞች ላይ ምራቅ በመትፋት ነበር።
ከጄራርድ ሁዬ ከጥናት ራዳር ያመለጠው ዲዩፍ በሶስት ዓመት የአንፊልድ ቆይታው ለቀዮቹ ማስቆጠር የቻለው 3 ግቦችን ብቻ ነው። ሊቨርፑል በሜዳ ላይ ጎል በሚፈልግባቸው ወሳኝ ጨዋታዎች ከተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች እና ደጋፊዎች ሳይቀር የሚገባበት ውዝግብ የቡድኑን ገጽታ ሲያበላሽ ቆይቷል።
በመርሲሳይድ የሶስት ዓመት ቆይታ የሚታወሰው በመርሲሳይድ ደርቢ የኤቨርተን ኳስ አቀባይ ህጻንን ነጫ ጭባ ብሎ በመሳደቡ በኤፍ ኤው በዘረኝነት የተከሰሰበት አጋጣሚ እና የቡድን አጋሮቹን ካራግር እና ጄራርድን ካልደበደብኩ ብሎ መገላገሉ ነው።
ጄራርድ ሁዬ ግለ ታሪካቸውን በጻፉበት መጽሃፍ በሊቨርፑል ቆይታዬ የሰራሁት ትልቁ ስህተት አል ሃጂ ዲዩፍን ማስፈረሜ ነው ሲሉ ጽፈዋል። ሊቨርፑል ተጫዋቹን ከሶስት ዓመት ያልተሳካለት ቆይታ በኋላ ለቦልተን ወንደረርስ አሰልፎ ሲሰጠው የቦልተኑ አለቃ ሳም አላርዳይስ ተጫዋቹን አስተካክለዋለሁ በሚል መተማመን ነበራቸው።
ቦልተን ተጫዋቹን በመጀመሪያ በውሰት በኋላም በቋሚ ዝውውር እስከ 2008 አቆይቶታል። በቆይታውም በተሰለፈባቸው 87 ጨዋታዎች 12 ጎሎችን ከመረብ አስርፏል። ቢግ ሳም የተጫዋቹን ጠባይ ተመልክተው የስነ ልቦና ባለሙያ ሊያየው ይገባል በማለት ተናግረው ነበር። ዲዩፍ በ2008 የክረምት የዝውውር ገበያ ወደ ሰንደርላንድ በመጓዝ የአንድ ዓመት ቆይታ አሳልፏል። በቆይታው አንድም ግብ ማስቆጠር ተስኖት ወደ ቀጣዩ ክለቡ ብላክበርን ሮቨርስ በ2009 ተጉዟል።
ከዚያም በኋላ ዲዩፍ ወደ ዶንካስተር ሮቨርስ፣ ሊድስ ዩናይትድ እና ወደ ሩቅ ምስራቅ ተጉዞ ለሳዑዲው ሳባህ ክለብ ተጫውቷል። በሄደባቸው ክለቦች ሁሉ ከአሰልጣኞች፣ ዳኞች፣ ደጋፊዎች እና ተጫዋቾች ጋር በመጣላት የጋዜጦች ወሬ ማግለብለቢያ ሲሆን ከርሟል።
በስኮትላንዱ ሬንጀርስ በነበረው ቆይታ እጅግ አደገኛ በሆነ ሃይማኖታዊ ጥላ በሚያጠላበት የሬንጀርስ እና ሴልቲክ የደርቢ ጨዋታ የሴልቲክ አሰልጣኝን ለመደብደብ በመሞከር እና ጸያፍ ስድብ በመሳደቡ ከፍተኛ ብጥብጥ እንዲነሳ ምክንያት ሆኖ ነበር።
ዲዩፍ ለሃገሬ እና በተጫወትኩባቸው ክለቦች ሁሉ አስደናቂ ነበርኩ ቢልም፣ አሁን ድረስ የሚታወሰው በአወዛጋቢ ድርጊቶቹ ነው። የቀድሞው አውዛጋቢ በአውሮፓውያኑ 2017 ወደ ፖለቲካው በመመጣት የዳካር ከተማ ከንቲባ ለመሆን ጥረት አድርጎ አልተሳካለትም። የፕሬዚዳንት ማኪ ሴል ስፖርታዊ ጉዳዮች አማካሪ በመሆን የራሱን ስፖርታዊ ጋዜጣ እና ጂምናዚየም አቋቁሟል።
አሁን ላይ ደግሞ በያዘው ስራ ላይ የሴኔጋል ሁለተኛ ዲቪዚዮን ተሳታፊ በሆነው ጎዲያዌ ክለብ በስፖርት ዳይሬክተር ሃላፊነት በመስራት ላይ ይገኛል።
በ-አልፈሪድ ነስሮ












