።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።
የጀርመን ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ቡድኑ የተሰጥኦ እጥረት አለበት የሚለውን ወሬ ውድቅ አድርገዋል። ሆኖም፣ ባለፉት አስርት ዓመታት በዋና ዋና ውድድሮች ላይ ያሳየው ደካማ ውጤት ግምት ውስጥ በማስገባት፣ አራት ጊዜ የዓለም ሻምፒዮን የሆነውን ቡድን ለማሻሻል ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ጀርመን በዓለም ዋንጫው በጥሎ ማለፍ ላይ በፓራጓይ ከተሸነፈች በኋላ፣ ክሎፕ በክረምቱ ወቅት ከጁሊያን ናግልስማን ቦታውን ተረክበዋል።
ይህም ጀርመን በ2018 እና በ2022 ከምድብ ድልድል ደረጃ ላይ ከተሰናበተች በኋላ፣ ከውድድሩ በጊዜ መውጣቷ ለሶስተኛ ጊዜ ተከታታይ ክስተት ሆኗል።
ዛሬ ምሽት ከሰርቢያ ጋር ከሚካሄደው የኔሽንስ ሊግ ጨዋታ አስቀድሞ በቤልግሬድ አስተያየታቸውን የሰጡት ክሎፕ፣ በእጃቸው ባለው የተሰጥኦ ክምችት ላይ እምነት እንዳላቸውና ተጫዋቾቹ አብረው ለመስራት ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል።
ክሎፕ ሲናገሩ፣ “የጀርመን እግር ኳስ በጥሩ ተጫዋቾች፣ በታላላቅ ተሰጥኦዎች፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ በሆኑ ተጫዋቾች እና በመሳሰሉት ረገድ ክፍተት እንዳለበት ብዙ ጊዜ ይነገራል” ብለዋል።
“ነገር ግን፣ እኔ ስለዚህ ቡድን በጣም አዎንታዊ አመለካከት አለኝ። እውነቱን ለመናገር፣ በጣም ጥሩ የሆነ ቅንጅት አለን።”
የ59 ዓመቱ ክሎፕ፣ “የዋህ ወይም ነገሮችን በግዴለሽነት የምመለከት አይደለሁም፤ በእርግጥም በጣም ጥሩ ቡድን አለን… ማድረግ ያለብን ነገር ቢኖር ይህንን በሜዳ ላይ በተግባር ማሳየት ብቻ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
የቀድሞው የሊቨርፑል አሰልጣኝ፣ በአንፊልድ ኃላፊነቱን ሲረከቡም ጊዜ ጠይቀው ነበር፤ በወቅቱ ክለቡን ወደ ቀድሞ ክብሩ ለመመለስ፣ በቡድኑ ላይ እምነት ያጡ ሰዎችን ወደ “አማኞች” (በቡድኑ የሚያምኑ) መቀየር እንደሚያስፈልግ ተናግረው ነበር።
ክሎፕ ሐሙስ ዕለት ሲናገሩ፣ “ለራሴ ጊዜ መስጠት አለብኝ” ካሉ በኋላ፣ “ይህ ለህዝቡ (ለደጋፊዎች) ተቀባይነት ይኖረው እንደሆነ ግን በእኔ ቁጥጥር ስር ያለ ነገር አይደለም” ሲሉ አክለዋል።
“በትክክለኛው መንገድ ላይ ነን፤ ምንም እንኳን ከግቡ ለመድረስ አሁንም ረጅም መንገድ ቢቀረንም። መሰረቱ ግን በእርግጥም ጥሩ ነው።”
ክሎፕ በቅርብ ሳምንታት ጥሩ ብቃት እያሳየ የሚገኘውን የሊቨርፑል አማካይ ፍሎሪያን ዊርትዝን አድንቀዋል።
“ፍሎ (ዊርትዝ) በጣም ጥሩ የአካልና የብቃት ሁኔታ ላይ ይገኛል።” “እሱ ለእኛ ትልቅ እገዛ ሊሆንልን ይችላል፣” ሲሉ ክሎፕ ተናግረዋል።
ዊርቲዝ እ.ኤ.አ. በ2025 ከፍተኛ የዝውውር ክፍያ ወደ ሊቨርፑል ከተዛወረ በኋላ ትችቶች ሲሰነዘሩበት ቆይቷል፤ ነገር ግን በአዲሱ የሊቨርፑል አሰልጣኝ አንዶኒ ኢራኦላ ስር አፈጻጸሙን ማሻሻል ችሏል።
ባለፉት አራት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ሶስት ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን ያቀበለ ሲሆን፣ እሁድ ዕለት ክሪስታል ፓላስን 3 ለ 1 ባሸነፉበት ጨዋታም በውድድር ዘመኑ የመጀመሪያ የሊግ ጎሉን አስቆጥሯል።
ቀደም ሲል ለባየር ሌቨርኩሰን ይጫወት የነበረው ይህ ተጫዋች ገና የ23 ዓመት ወጣት ቢሆንም፣ ሰኞ ዕለት በበርሊን ለጀርመን ብሔራዊ ቡድን 50ኛ ጨዋታውን ሊያደርግ ይችላል።
ዊርቲዝ ቡድኑ በክሎፕ ስር መሻሻል እያሳየ እንደሆነ የተሰማው ሲሆን፣ በወጣቱ ስብስብ ውስጥ የበለጠ የመሪነት ሚና መውሰድ እንደሚፈልግም ገልጿል።
“ቡድኑ ይበልጥ ተቀናጅቷል፤ እንዲሁም በልምምድ ወቅት ስንሰራባቸው የነበሩ ነገሮች ይበልጥ ጠንካራ ሆነዋል። ዋናው ቁምነገር ቁርጠኝነትን፣ እምነትን እና ፍላጎትን ወደ ሜዳ ይዞ መግባት ነው፣” ሲል ዊርቲዝ ሐሙስ ዕለት ተናግሯል።
በ-ሳምሶን አበበ
። ። ።
ማስፈንጠሪያውን (ሊንኩን) በመጫን NBC ኢትዮጵያን ይጎብኙ ይወዳጁ
https://linktr.ee/NBCEthiopiaTV
#NBCEthiopia
#ሆኖ_መገኘት
#Ethiopia












