ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የምታደርገው ጥረት ህጋዊ መሰረት ያለው ብሔራዊ ፍላጎት መሆኑን እና ተገቢውን ዕውቅና ማግኘት እንዳለበት የቀድሞው የኮትዲቯር ጠቅላይ ሚኒስትር እና የሀገሪቱ የሕዝባዊ ግንባር (FPI) ፕሬዝዳንት ፓስካል አፊ ንጌሳን ገለጹ።
የኢትዮጵያ ፍላጎት ቀጣናውን የጋራ ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ በውይይት እና በስምምነት ምላሽ ማግኘት እንደሚገባም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ከሰፊው ጂኦፖለቲካዊ ሁኔታና ከአፍሪካ ቀንድ ሀገራት የጋራ መፃኢ ዕድል አንጻር መቃኘት እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ፍላጎት በሁሉም ወገኖች ዘንድ ተቀባይነት ባለው መንገድ እንደሚፈታ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
በመሆኑም በጉዳዩ ላይ የሰከነ እና ገንቢ ውይይት ማድረግ እንደሚገባም ጠቅሰው፤ አፍሪካዊ መፍትሔዎች ለዘላቂ ሰላም እና ብልጽግና ወሳኝ ናቸው ብለዋል።
አፍሪካ ማደግ የምትችለው በአንድነት ነው፤ እውነተኛ አንድነት ደግሞ በሀሳብና በሀብት መጋራት ሊገለጽ ይገባል ብለዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያን የባህር በር የማግኘት ፍላጎት ከዚህ ማዕቀፍ አንጻር ማየት እንደሚገባም ነው የቀድሞው የኮትዲቯር ጠቅላይ ሚኒስትር እና የሀገሪቱ የሕዝባዊ ግንባር (FPI) ፕሬዝዳንት ፓስካል አፊ ንጌሳን የተናገሩት።














