በካይሮ በቴሌኮም ህንፃ ላይ በተነሳ የእሳት ቃጠሎ የ4ሰዎች ህይወት ሲያልፍ የበረራ አገልግሎቶች ተቋርጠው ቆይተዋል፡፡
በግብፅ ካይሮ በዋና የቴሌኮም ህንፃ ላይ በተነሳ የእሳት ቃጠሎ ቢያንስ 4 የድርጅቱ ሰራተኞች ህይወት ሲያልፍ 27 ሰዎች ቆስለው ሆስፒታል መግባታቸውን የኩባንያው የሰራተኞች ማህበር በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሆሳም አብደል ጋፋር ለአሶሼትድ ፕሬስ እንደተናገሩት በጭስ በመታፈን የተጎዱትን ጨምሮ የተጎጂዎች ቁጥር ከ14 ወደ 27 ከፍ ብሏል።
ባለ 10 ፎቅ የቴሌኮም ህንጻው ላይ የተነሳው እና ለመቆጣጠር ሰአታት የፈጀው የእሳት አደጋ፣ በፎቅ ላይ ከሚገኙት አዳራሾች በአንዱ ተነስቶ ወደ ሌሎች የህንጻው ክፍሎች መዛመቱን የአካባቢው ባለስልጣናት አስታውቀዋል፡፡
በዓለም ዙሪያ ያለውን የኢንተርኔት አገልግሎትን የሚከታተለው ድርጅት ኔትብሎክስ አደጋውን ተከትሎ አደጋውን ተከትሎ የኢንተርኔት እና የሞባይል ስልክ አገልግሎት በጊዜያዊነት ተቋርጦ እንደነበር የገለጸ ሲሆን፣ በሀገሪቱ ብሄራዊ ትስስር ከመደበኛ ደረጃዎች ወደ 62በመቶ ዝቅ ብሏል፡፡
የኢንተርኔት መቆራረጡ የአየር ትራፊክን አቋርጦ እንደነበር እና ማክሰኞ ማለዳ ላይ ሁሉም የቆሙ በረራዎች መጀመራቸውን የሲቪል አቪዬሽን ሚኒስቴር አስታውቋል።
በ-ሰላማዊት ወንድወሰን












