የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያጠናቀቃቸውን በ11 ክፍለ ከተሞች የተገነቡት እና ከ5 ቢለዬን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸዉ 122 የስፖርት ማዘውተሪያ እንዲሁም 1,155 የህፃናት መጫወቻ ማዕከላትን በአጠቃላይ 1277 ፕሮጀክቶችን ለአገልግሎት ክፍት ተደርገዋል።
አገልግሎቱ ለህዝብ ክፍት መደረጉን ተከትሎ መልእክታቸውን ያስተላለፉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ “በአዕምሮና በአካል የዳበረ ትውልድ ለመገንባት ከከተማችን ሀብት መሬት እና በጀት፤ ከእኛ ከአመራሮች እና ከሰራተኛው ደግሞ ጉልበት እና ጊዜ እፍታውን ወስደን እንዲሁም ማህበረሰቡን በማስተባበር ለትውልዱ ቅድሚያ ስጥተን ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገን ገንብተናል” ነው ያሉት።
የስራ ቦታዎች እና የመኖሪያ አካባቢዎችን ከግምት በማገባት በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸው፣ ባለፉት ሶስት ዓመታት በአጠቃላይ 3 ሺህ 789 የህፃናት የመጫወቻ ማዕከላትን እና 1 ሺህ 530 የስፖርት ማዘውተሪያዎች ተገንብተው አገልግሎት መስጠታቸውን አስታውሰዋል።
ፕሮጀክቶቹ ሲገነቡ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ከፍተኛ እንደነበረ የጠቀሱት ከንቲባዋ፣ የመሰረተ ልማቶቹ 50 በመቶ ወጪ የተሸፈነዉ በማህበረሰቡ መሆኑ ልዩ ያደርጋቸዋል ብለዋል።
“ለወጣቶችና ህጻናት የስፖርት ማዘውተሪያና መጫወቻ ማዕከላትን ለመገንባት ስናደርገው በነበረው ጥረት ሁሉ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱና ላስተባበሩ አካላት ምስጋናዬን አቀርባለሁ።” ማለታቸውን የከንቲባ ጽ/ቤት ያደረሰን መረጃ ያመለክታል።












