ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ጉባኤ (COP 31) ላይ የነበራት ተሳትፎ እና የቀጣይ ዓመት ዝግጅት

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአንታልያ ቱርክዬ በተካሄደው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ ተሳትፈዋል። በቆይታቸውም ከተለያዩ የዓለም መሪዎች ጋር ስኬታማ የሁለትዮሽ ውይይቶችን አድርገዋል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ በሚቀጥለው ዓመት የዚህ ታላቅ ጉባኤ (COP 32) አስተናጋጅ ሀገር እንደመሆኗ ዝግጁነቷን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አስታውቀዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ከአንታልያ እንደገለጹት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቆይታቸውን የጀመሩትም ከቱርክዬው ፕሬዝዳንት ረጅብ ጣይብ ኤርዶሃን ጋር በመወያየት ነው። በውይይታቸውም ቀደም ሲል የተደረጉ የዲፕሎማሲና የኢኮኖሚ ትብብር ስምምነቶችን አፈጻጸም ገምግመዋል። ኢትዮጵያ በቀጣዩ ዓመት የምታስተናግደውን ጉባኤ አስመልክቶ ከቱርክዬ ልምድና ድጋፍ በምታገኝበት ሁኔታ ላይም መምክራቸውን ሀላፊዋ አብራርተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዋናው ጉባኤ ጎን ለጎን ከተለያዩ መሪዎች ጋር ውይይት አድርገዋል። ከኖርዌይ፣ ከፊንላንድ፣ ከባርቤዶስ፣ ቦትስዋና እና ከሶማሊያ መሪዎች ጋር በመምከር የቀድሞ የትብብር አጀንዳዎች ያሉበትን ደረጃ መፈተሻቸውን ቢልለኔ ገልጸዋል።
በዋናው የመሪዎች ጉባኤ መክፈቻ መድረክ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እንደ ቀጣይ የጉባኤው አስተናጋጅ ሀገር መሪ ንግግር አድርገዋል። በንግግራቸውም ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ መሆኗን አንስተዋል። በድርቅና በጎርፍ የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመቀነስ የሜትሮሎጂ ትንበያ ሥርዓቷን በማዘመንና ህብረተሰቡ በምን መልኩ መዘጋጀት እንዳለበት የሚያመለክቱ ቅድመ ዝግጅት እያደረገች መሆኗን አብራርተዋል።

ባለፉት ስምንት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ከ56 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ማንሳታቸውን ቢልለኔ ገልጸዋል። ይህ ተግባር የአካባቢ ጥበቃን ከማረጋገጥ ባለፈ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ የሆነውን የኢትዮጵያ ቡና ምርት ለመታደግ ይረዳል ነው ያሉት። የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎችን ለማጠናከርም ትልቅ ተስፋ ሰጪ እርምጃ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው መናገራቸውን አክለዋል።
በተጨማሪም በጉባኤው የተዘጋጀው ሀገርን ማስተዋወቂያ መርሃ ግብር (ፓቪሊየን) ላይ ኢትዮጵያን ማስተዋወቂያ አምዶች በስፋት መቅረባቸውን ሀላፊዋ ገልጸዋል። በዚህም የቡና እና የሰው ዘር መገኛ አልፎም የአትሌቶች እና የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምድር መሆኗን ከዚህም በተጨማሪ በበርካታ ማሳያ አምዶች ኢትዮጵያውያን በስፋት ሀገራቸውን እያስተዋወቁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ወጣት ተደራዳሪዎች በጉባኤው ላይ እየተሳተፉ የኢትዮጵያን ብሎም የአፍሪካን አቋም በብቃት እያንጸባረቁ መሆናቸውን አብራርተዋል።
ቢልለኔ ስዩም በቀጣዩ ዓመት አዲስ አበባ የምታስተናግደውን ታላቅ ዓለም አቀፍ ጉባኤ በስኬት ለማጠናቀቅ ከሆቴልና ከትራንስፖርት እስከ ቱሪዝምና አገልግሎት ዘርፍ የሁሉም ርብርብ ያስፈልጋል ብለዋል።
አክለውም ከመንግስት ዝግጅት ባሻገር የመዲናዋ ነዋሪዎች እና የግል ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ኢትዮጵያዊ እንግዳ ተቀባይነትን በተግባር በማሳየት የጋራ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በ – የአብስራ ተፈራ










