በዓለም ዙሪያ በርካታ ቱሪስቶች ብርቅዬ የወፍ ዝርያዎችን ለመጎብኘት ወደ ተለያዩ ሃገራት ይጓዛሉ። ይህ የጎብኚዎች ፍላጎት ለብዙ ሃገራት ከፍተኛ የቱሪዝም ሃብት እንደሆነ ይነገራል።
ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ከታደለቻቸው ፀጋዎች መካከል ሰፊ የወፍ ዝርያ ሀብት ቢኖራትም፣ ይህንን አቅም ወደ ዓለም አቀፍ የቱሪዝም መስህብነት በመቀየር ረገድ ገና ብዙ የሚቀራት ሥራ እንዳለ ይነሳል።
በNBC ኢትዮጵያ የ”ስለ ቱሪዝም” ፕሮግራም ላይ ቆይታ ያደረጉት የአእዋፉት አስጎብኚው አቶ አቤል በላይ፣ ኢትዮጵያ በወፍ ቱሪዝም ዘርፍ ካላት እምቅ አቅም አንጻር የዘርፉ እድገት አነስተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም ወፎችን በማወቅ፣ በመመልከትና ለጎብኚዎች በማስጎብኘት ሥራ የተሰማሩ ባለሙያዎች ቁጥር ጥቂት መሆኑ ለዘርፉ እድገት ማነቆ እንደሆነም አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ለወፍ ጎብኝዎች እጅግ ምቹ የሆነች ሃገር ናት፡፡ እንደ አቤል ገለጻ፣ በመጽሐፍት የተጠቀሱ የወፍ ዝርያዎች ቁጥር የሃገሪቱን እውነተኛ ሀብት ሙሉ በሙሉ እንደማያሳይ ተናግሯል። በግላቸው ባካሄዱት ጥናት እንዳስተዋሉ፣ በተለመዱት የወፍ መረጃ መጽሐፍት ያልተካተቱ ነገር ግን ዓመቱን ሙሉ በሃገሪቱ የሚገኙ በርካታ ዝርያዎች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ ይህም በኢትዮጵያ የወፍ ሀብት ላይ ተጨማሪ ሳይንሳዊ ጥናት እንደሚያስፈልግ ማሳያ ነው ብለዋል።
እንደ አቶ አቤል ገለጻ፣ ኢትዮጵያ አምስቱንም የስነ-ምህዳር አይነቶች ባለቤት በመሆኗ፣ ለብዙ የወፍ ዝርያዎች ምቹ መኖሪያ እንድትሆን እንዳስቻላት አንስተው፣ ይህም አንድ ጎብኚ በአነስተኛ የጉዞ ርቀት ውስጥ በርካታ ዝርያዎችን እንዲመለከት ያግዘዋል ነው ያሉት። በተለይም ከፍተኛ የጉዞ ወጪ ሳያወጡ የተፈጥሮ ሀብቶችን ለመጎብኘት ለሚፈልጉ ቱሪስቶች ይህ ትልቅ እድል እንደሆነ ተናግረዋል።
የወፍ ቱሪዝም አቅም በክልሎችና በተፈጥሮ ፓርኮች ብቻ አይወሰንም ያሉት አስጎብኚው፣ አዲስ አበባም ከ12 በላይ ብርቅዬ የወፍ ዝርያዎችን የያዘች መሆኗን ገልጸዋል። እንደ ጊዮን ሆቴል፣ ፒኮክ የቀድሞው ብሔረ ጽጌ እና በኦልድ ኤርፖርት አካባቢ የሚገኙ ረግረጋማ ቦታዎች የወፍ ተመልካቾችን ሊስቡ የሚችሉ መዳረሻዎች እንደሆኑም ጠቁመዋል።

ሆኖም እነዚህ ቦታዎች ያላቸው አቅም በተገቢው መንገድ እንዳለማ አቶ አቤል ገልጸው፣ ከዚህ አንፃር ኬንያና ታንዛኒያ የተፈጥሮ ሀብታቸውን በተገቢው መንገድ በማልማት ረገድ እንደሚበልጡን አንስተዋል። በመሆኑም የሃገሪቱን የወፍ ሀብት በመለየት፣ የጉብኝት መስመሮችን በማዘጋጀትና በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ በተቀናጀ መንገድ ማስተዋወቅ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
እንደ አቶ አቤል ምልከታ፣ እነዚህ ጎብኚዎች ያነሷቸውን ፎቶግራፎች ይዘው ወደ ሃገራቸው ሲመለሱ ስለ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብት በተለያዩ መድረኮች ያስተዋውቃሉ። ይህም የሃገሪቱን ገጽታ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማሳደግ የሚያግዝ ተጨማሪ እድል እንደሆነ አንስተዋል።
በፕሮግራሙ ላይ ትኩረት የተደረገበት ሌላውኛው ጉዳይ የባለሙያዎች አቅምና የእውቀት ክፍተት ነው።የወፍ ቱሪዝም ስለ ወፎች ዝርያ፣ መኖሪያ አካባቢና የእንቅስቃሴ ሁኔታ ጥልቅ እውቀት ይጠይቃል ያሉት አቶ አቤል፣ በተለይ በብሔራዊ ፓርኮች የሚሠሩ ሬንጀሮችና አስጎብኚዎች ስለ ወፎችና ስለ ስነ-ምህዳሩ ያላቸው እውቀት ሊጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል። በዘርፉ የሚሰማሩ ሰዎችን በተከታታይ ስልጠና ማብቃትና በትምህርት ስርዐት ውስጥም ስለ ሃገሪቱ ብርቅዬ አእዋፋት የሚሰጠውም ትኩረት ማሳደግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በዓለም ላይ በተወሰኑ አካባቢዎች ብቻ የሚገኙ ብርቅዬ የወፍ ዝርያዎች ይገኛሉ ያሉት አስጎብኚው ፣ እነዚህ ዝርያዎች ለተፈጥሮ ተመራማሪዎችና ጎብኝዎች ልዩ መስህብ መሆናቸውን ተናግረዋል። ከዚህ ባለፈም እንደ ወለጋና ባሌ ያሉ ገና በበቂ ሁኔታ ያልተጠኑ አካባቢዎች እንዳሉ አንስተው፣ በእነዚህ ሥፍራዎች ተጨማሪ ጥናት ማካሄድ አዳዲስ ዝርያዎችን ለማግኘትና የሃገሪቱን የተፈጥሮ ሀብት በተሻለ ሁኔታ ለመረዳት እንደሚያግዝ አንስተዋል።
እንደ አቶ አቤል ገለጻ፣ የወፍ ቱሪዝምን ለማሳደግ ባለሙያዎች ተገቢውን የሜዳ መነጽር፣ የፎቶግራፊ መሳሪያዎችና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ማግኘት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡ እነዚህን መሳሪያዎች ከውጭ ለማስገባት የሚያጋጥሙ ችግሮች እንዲፈቱና ለዘርፉ ተቋማዊ ድጋፍ እንዲደረግም ጥርያቸዉን አቀርበዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ከብሔራዊ ፓርኮች እስከ ኤምባሲዎች ድረስ ያለው ትብብር መጠናከር እንዳለበት ገልጸው፣ እንደ ሩዋንዳ ያሉ ሃገራት የወፍ ፌስቲቫሎችን በማዘጋጀት የሚያከናውኑትን ሥራ በመመልከትም ተሞክሮ መውሰድ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የወፍ ቱሪዝም ለኢትዮጵያ የተፈጥሮ ውበትን ከማስተዋወቅ በላይ የሥራ ዕድል የሚፈጥር፣ የውጭ ምንዛሬ ገቢን የሚያሳድግና የሃገሪቱን ዓለም አቀፍ ገጽታ የሚያጎለብት ዘርፍ ነው። ይህንን እምቅ አቅም ወደ ተጨባጭ ውጤት ለመቀየር የግለሰቦች ጥረት ብቻ ሳይሆን የመንግሥት፣ የቱሪዝም ተቋማት፣ የምርምር ማዕከላትና የግሉ ዘርፍ የጋራ ትብብር እንደምያስፈልግ አቶ አቤል ገልጸዋል። ሀብቱን መለየት፣ መጠበቅና በተገቢው መንገድ ለዓለም ማቅረብ ከተቻለ፣ ኢትዮጵያ በወፍ ቱሪዝም ቀዳሚ የአፍሪካ መዳረሻ የመሆን እድሏ ከፍተኛ እንደሆነም ተመላክቷል።
በ- በረከት አስረስ












