ኢትዮጵያ ታሪካዊ ቅርሶች፣ የተለያዩ ባህሎችና ውብ የተፈጥሮ ሀብቶች ያሏት ሀገር ናት። እነዚህን ሀብቶችን ለዓለም በማስተዋወቅ ከቱሪዝም የሚገኘውን ጥቅም ማሳደግ የዘርፉ ዋነኛ ተግባር መሆን አለበት። በተለይ COP 32ን ለማስተናገድ የምታደርገው ዝግጅት ለሀገሪቱ አዲስ ዕድሎችን ፈጥሯል።

በNBC Ethiopia «ስለ ቱሪዝም» ፕሮግራም ላይ እንግዳ ሁኖ የቀረቡት የአዲስ አበባ ሆቴልና ቱሪዝም ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ አሸናፊ ሙሉጌታ፣ ኢትዮጵያ ጥሩ የእንግዳ አቀባበል ባህል መገንባት እንዳለባት ተናግረዋል።

ጥሩ ሆቴልና ዘመናዊ ሕንፃ መገንባት ብቻ በቂ አይደለም ያሉት አቶ አሸናፊ፤ ሠራተኞች በቂ ስልጠና ማግኘት እንዳለባቸውና መንግሥትም ለቱሪዝም ዘርፉ ምቹ ፖሊሲዎችን መቅረጽ እንዳለበት ገልጸዋል ።
እንግዶች ወደ ሀገር ሲገቡ የሚያገኙት የመጀመሪያ አገልግሎት ስለ ሀገሪቱ የሚኖራቸውን እይታ ይወስናል። ስለዚህ የታክሲ ሾፌሮች፣ የሆቴል ሰራተኞችና ከጎብኚዎች ጋር የሚሰሩ ሌሎች አካላት የእንግዳ አቀባበል ላይ ተገቢውን ስልጠና መውሰድ እንዳለባቸውም ተነስቷል።

COP 32 ለሀገሪቱ የሚያመጣው ጥቅም ዘርፈ ብዙ እንደሆነ አንስተው፣ ይህ ጉባኤ ከፍተኛ የሆነ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥና የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የበለጠ እንደሚያሳድግ አንስተዋል።
ሆኖም በጉባኤው ወቅት የሚከሰቱ ያልተገቡ የዋጋ ጭማሪዎች በጥንቃቄ መታየት አለበት ያሉት ሃላፊው፣ ይሄ ተግባር የሀገሪቱን ገጽታ ሊጎዳና የተሳታፊዎችን የጊዜ ቆይታ ሊያሳጥር እንደሚችልም ጠቁመዋል።
በሚቀጥለው ዓመት የሚካሄደው ይህ ጉባኤ ውጤታማ እንዲሆን፣ በመንግሥት ወይም በሆቴሎች ብቻ የሚወሰን አይደለም፡፡ ሁሉም ዜጋ የራሱን ድርሻ በመወጣትና ለእንግዶች ጥሩ አገልግሎቶችን በመስጠት ሃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪያቸውን አስተላልፈው፣ ከCOP 32 በኋላም ኢትዮጵያ ተጨማሪ ዓለም አቀፍ ሁነቶችን እንድታስተናግድና የቱሪዝም ዘርፏን እንድታሳድግ ያግዛል ነው ያሉት፡፡












