
በኤንቢሲ ኢትዮጵያ ጊዜ ግስ መርሀግብር ላይ ቆይታ ያደረጉት ጀነራል ባጫ ደበሌ የትግራይን ህዝብ ወደ ቀድሞው ሰላማዊና የተረጋጋ ህይወቱ ለመመለስ ሁሉን አቀፍ የመልሶ ማቋቋም ስራዎች ሊከናወኑ እንደሚገባ ገለጹ ።
በቆይታቸው፣ ክልሉን ከነበረበት የውድቀት አዙሪት ለማውጣት እና ህዝቡን በዘላቂነት ለማረጋጋት ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮችን አንስተዋል።
ጀነራሉ እንደገለጹት ፣ ቀደም ሲል በክልሉ የተከሰተው ጦርነት በአጭር ጊዜ ውስጥ የተጠናቀቀ ቢሆንም፣ የህብረተሰቡን አስተሳሰብ እና የሰላም ግንዛቤ ለመለወጥ ግን ጊዜ ሊወስድ ይችላል ብለዋል ።
ህዝቡን በማረጋጋት ወደ ነበረበት ሰላማዊና ማህበራዊ ህይወት ለመመለስ የተቀናጀ የመልሶ ማቋቋም ስራ በግንባር ቀደምትነት መከናወን እንዳለበትም ጠቁመዋል ።

በሌላ በኩል የቀሩ ታጣቂዎች ከጥፋት ጎዳና በመውጣት ትጥቃቸውን እንዲፈቱ እና የሰላም አማራጮችን እንዲከተሉ አሳስበዋል ። አሁን ላይ ሁሉም የጥፋት ኃይሎች ተበትነዋል ያሉት ጀነራሉ፣ የቀሩትም በአጭር ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ትጥቅ የማስፈታት ስራው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመላክተዋል።
የፖለቲካ የበላይነት አስተሳሰብና የጥላቻ ትርክትን ከትግራይ ህዝብ እስከወዲያኛው ማስወገድ እንደሚያስፈልግም በውይይቱ ላይ አንስተዋል ።
የክልሉን ህዝብ ስም በመጠቀም የሚደረጉ ፀረ-ሰላም እና የጥፋት ፖለቲካ አቀንቃኝ አካሄዶችን በማክሸፍ፣ ማህበረሰቡን ከጠባብ የፖለቲካ ፍላጎት ነፃ ማውጣት ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል ።
አክለውም በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ፋብሪካዎችና የኢንቨስትመንት ተቋማት በሻዕቢያ እና በክልሉ ውስጥ በሚገኙ ካድሬዎች መዘረፋቸውን ጠቅሰው እነዚህን መልሶ ማቋቋም ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል።
በ- ታደለ ገበየሁ












