ህወሓት ለግብፅና ለሻዕቢያ ጥቅም የሚሠራ፣ ኢትዮጵያንም ለማዳከም የውጭ ኃይሎችን ተልዕኮ የሚፈጽም ህገወጡ ቡድን ነው ሲሉ ጀነራል ባጫ ደበሌ ተናገሩ። ጀነራሉ ህወሓት ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚከሰቱ ግጭቶች ዋነኛ ምንጭ እንደሆነ በመግለጽ፣ የህገወጡን ቡድን አመሰራረት፣ የፖለቲካ አቋምና ከትግራይ ሕዝብ ጋር ያለውን ግንኙነት በተመለከተ ሃሳባቸውን አካፍለዋል።

አምባሳደር ጀነራል ባጫ ደበሌ በNBC ኢትዮጵያ የ”ጊዜ ግስ” ፕሮግራም ላይ በነበራቸው ቆይታ ስለህወሓት ያልተሰሙና አዳዲስ ሃሳቦችን አንስተዋል።
ድርጅቱ የሀገሪቱን ችግሮች በማባባስ ውስጥ የሚጫወተውን ሚና ጀነራሉ ሲያብራሩ፣ ለውጭ ኃይሎች የሚሠራና የሀገርን ጥቅም አሳልፎ የሚሰጥ ባንዳ እንደሆነ ይገልፃሉ።
ፅንፈኛ ኃይሉ በ1967 ዓ.ም. ሲመሠረት የትግራይን ሕዝብ ነፃ ለማውጣት ሳይሆን ከሻዕቢያና ከግብፅ የተሰጠውን ተልዕኮ ለማስፈጸም የተቋቋመ መሆኑን ጀነራሉ አንስተው፣ የጥፋት ኃይሉ የወንጀል ተግባራት ውስጥ የተዘፈቀና የፖለቲካ ሁኔታዎችን በትክክል መገምገም የማይችል አቅመቢስ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል የህወሓትን አመራርና ካድሬዎች ከትግራይ ሕዝብ ለይቶ ማየት እንደሚገባ ያስገነዘቡት ጀነራል ባጫ፣ ሕዝቡ ጦርነት የማይፈልግና ለሰራዊቱ እንጀራና ውሃ ሲሰጥ የነበረ ሩህሩህ ህዝብ ነው ብለዋል።
የህገወጡን ቡድን አስተሳሰብ በተመለከተም፣ የህወሓት ካድሬዎች ከኮሚኒዝምና ከጽንፈኛ ብሔርተኝነት የተወሰዱ አስተሳሰቦችን በማቀናጀት ፋሺስታዊ ባህሪ የተላበሱ እንደሆኑ ጀነራሉ ያነሳሉ። ካድሬዎቹ የሃይማኖትንና የሞራል ገደቦችን የማያከብሩ መሆናቸውንም በመጥቀስ፣ ይህ አስተሳሰብ በህገወጡ ቡድን አካሄድ ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ ከፍተኛ እንደሆነ አመላክተዋል።
ህወሓትና መሰል ኃይሎች ከውጭ ጠላቶች ጋር በመተባበር የኢትዮጵያን አንድነትና ሉዓላዊነት ለመጉዳት እንደሚንቀሳቀሱ ያነሱት ጀነራሉ ፣ ኢትዮጵያ ግን ከእነዚህ ፈተናዎች በላይ የሆነ ጽናትና የአንድነት አቅም እንዳላት ተናግረዋል።
በ-በረከት አስረስ













