
በኤንቢሲ ኢትዮጵያ “ጊዜ ግስ” ፕሮግራም ላይ በነበራቸው ቆይታ የቀድሞው በኬንያ የኢትዮጵያ ኢምባሲ አምባሳደር ጀነራል ባጫ ደበሌ፥ ህወሓት ሃገሪቱን ወደ ተደጋገመ የጦርነት አዙሪት ያስገባበትን ምክንያቶች በማንሳት ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ጀነራሉ እንደገለጹት ይህ የሽብር ቡድኑ በተደጋጋሚ ጦርነቶችን የመለኮሱ መሠረታዊ ምክንያት በራሱ ነፃ ውሳኔ ላይ ተመስርቶ ሳይሆን በውጪ ኃይሎች ቅጥረኝነት እና ተላላኪነት ላይ የመነጨ ነው።
ለበርካታ ህዝብ እልቂት ምክንያት የሆኑት በህወሓት የተጀመሩት ጦርነቶች የተከሰቱበትን መሠረታዊ ምክንያት ሲያብራሩ፥ ህወሓት የራሱ የሆነ ነፃ የፖለቲካ ውሳኔ ማሳለፍ የማይችል “የወጣለት ቅጥረኛ” ነው፡፡ ጀነራሉ አክለውም፣ ጦርነቱን የሚያቆመውም ሆነ የሚጀምረው በራሱ ፍላጎት ሳይሆን የኢትዮጵያን ሰላም የሚጠሉ ፀብ ጫሪ ቡድኖች በሚሰጡት ተልእኮ መሠረት መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም የዚህ ህገወጥ ቡድን አመራሮች በሀገሪቱ ላይ ከፍተኛ ወንጀልና ዝርፊያ የፈጸሙ በመሆናቸው በሰላማዊ መንገድና በሕግ አሠራር መኖር ስለማይችሉ፣ ሀገር በማፍረስ ወይም በውጪ ኃይሎች ግፊት በጥፋት ውስጥ ለመቆየት መምረጣቸውን ገልጸዋል።
መንግሥት ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ለህወሓት የጥሞና ጊዜ በመስጠት ወደ መግባባት እንዲመጡ የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደረገ ቢሆንም፤ የኢትዮጵያ ጠላቶች ግን ከውጪ ሆነው ትዕዛዝ በመስጠታቸው በተደጋጋሚ ጥቃቶችን ከመፈጸም አልተቆጠቡም ብለዋል፡፡ የጥፋት ቡድኑ ከውጪ ኃይሎች በኩል የተቀበላቸውን በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ድሮኖች እና የጦር መሳሪያዎች ገና ፈትቶ እንኳን ሳያይ ብሎም ሳይጠቀም በጥድፊያ ወደ ጦርነት በመግባቱ ያልጠበቀው ሽንፈት እንዳጋጠመው አብራርተዋል።
ጀነራሉ ህወሓት የትግራይን ሕዝብ እንደ ምሽግ በመጠቀም ለረጅም ጊዜ ሲንቀሳቀስ ቢቆይም፥ አሁን ላይ ህዝቡ የዚህን የሽብር ቡድን አጥፊነት፣ ሰላም ጠልነት እና ሃገርን የመከፋፈል የቅዠት ምኞት ተረድቶ እንደ ከዚህ ቀደሙ ከጎኑ መቆሙን ትቶ እርዳታውን በመንፈጉ፥ ቡድኑ ተመልሶ እንዳያንሰራራ ሆኖ መውደቁን ተናግረዋል።
በ – የአብሥራ ተፈራ












