
“በአማራ ህዝብ ላይ ትልቅ ስብራት ያመጡት” ሻዕቢያ እና ህወሓት መሆናቸውን የቀድሞው የጎጃም ፋኖ ቃል አቀባይ አቶ ማርእሸት ፀሐዩ በNBC ኢትዮጵያ “ጊዜ ግስ” ፕሮግራም ላይ በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡
በአማራ ክልል ስላለው ወቅታዊ ጉዳይ እና ስለ እኩይ ኃይሎች ያልተሰሙ አዳዲስ መረጃዎችንም አካፍለዋል፡፡
አቶ ማርእሸት የህገወጦቹን ጥምረት አስመልክተው ሲናገሩ፣ አንበሳ መጣብን ብለው በተጣመሩት ጅቦች መስለው ይገልጻሉ። አክለውም ቀደም ሲል ለበርካታ የፋኖ አመራሮች የአሁኑ ሁኔታ እንደሚከሰት ያስረዱ እንደነበር ጠቁመዋል። ህወሓት የትግራይን ህዝብ ሀብት ኤርትራ ይዞ እንደሚሄድ እንዲሁም ሻዕቢያ እነ ዘመነ ካሴን እና ደብረጽዮን ለራሱ የፖለቲካ ጥቅም ሲል አፍኖ እንደሚያስቀራቸው በማስገንዘብ ጥምረቱ ፈጽሞ የማያስፈልግ መሆኑን አስጠንቅቀው እንደነበር ያስታዉሳሉ።

በተጨማሪም ታሪካዊ ጠላቶቻችን የሆኑት የውጭ ኃይሎች በሚዲያ አማካይነት ወጣቱ ላይ አሉታዊ አመለካከት መፍጠራቸውን አንስተዋል። አያይዘውም እሳቸውም የዚህ የተሳሳተ አመለካካት ሰለባ እንደነበሩ አስታውሰው፣ በሚዲያ ሲነዛ የነበረው ነገር እውነት እንዳልሆነ በመረዳታቸው ወደሰላማዊ መንገድ እንደመጡ ተናግረዋል።
እነዚህ የዉጭ ሃይሎች የአማራ ልሂቃን የጋራ ህብረትና አንድነት እንዳይኖራቸው በማድረግ አጀንዳ ተቀባይና አስፈፃሚ አደርጓቸዋል ነው ያሉት። እንደ እሳቸው ገለጻ፣ እነዚህ አካላት ወጣቱን ጭምር በፍቅር እና በአንድነት ምትክ በቃላት ተቃርኖ እና በጥላቻ እንዲሳቡ በማድረግ ረገድ አጥፊ ሚና እንደነበራቸው ጠቁመዋል።
ልሂቃኑና ወጣቱ ሰከን ብሎ ማስተዋል እንደሚገባውና አስታራቂ ሃሳቦችን ይዞ ወደ ሰላምና ንግግር እንዲመጣ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ሙሉ ቃለ ምልልሱንና ዝርዝር ውይይቱን በቅርብ ቀን በNBC ኢትዮጵያ የ”ጊዜ ግስ” ፕሮግራም ላይ ይጠብቁን።
በ- በረከት አስረስ












