
የቀድሞ የህወሓት አባል ኮለኔል ገብረዋህድ ሀይሉ (ወዲጎዐይ) ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው ትግርኛ ተናጋሪ ዳያስፖራ የህወሓትን አካሄድና አሰራር እንደማይደግፍ ገለጹ።
በኤንቢሲ ኢትዮጵያ “ጊዜ ግስ” ፕሮግራም ላይ ቆይታ ያደረጉት ኮለኔል ገብረዋህድ ሀይሉ ስለወቅታዊው የትግራይ ክልል ሁኔታ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።

ከህዝቡ ፍላጎት ጋር የተያያዙ ነጥቦችን ሲያነሱ፣ በአሁኑ ወቅት ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው ትግርኛ ተናጋሪ ዳያስፖራ የህወሓትን አካሄድና አሰራር እንደማይደግፍና ቀሪውም በመጨረሻው የተስፋ መቁረጥ ምእራፍ ላይ መሆኑን አስረድተዋል።
ዳያስፖራው ማኅበረሰብ ቀደም ሲል ለድርጅቱ ያደርጉት ለነበረው ትብብርና ድጋፍም ይቅርታ መጠየቃቸውን የገለጹት ኮሎኔሉ፣ የዚህም ምክንያት ህብረተሰቡ አሁን የሚፈልገው ሰላም፣ ትምህርት፣ ልማትና በህይወት የመኖር መብቱን ማረጋገጥ እንደሆነ አብራርተዋል።
በትግራይ ክልል የሚገኙ ወታደራዊና ፖለቲካዊ አመራሮች አሰራርና አቅጣጫን በተመለከተ ከባድ ትችት ያቀረቡ ሲሆን፣ በክልሉ ያለውን ህዝባዊ እንግልትና ስቃይ የፈጠሩት እንዲሁም በህብረተሰቡ ላይ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መዛባት ያደረሱት በክልሉ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የጥፋት ኃይሎች መሆናቸውን ተናግረዋል ።
እንደ አመራሩ ገለጻ፣ የህወሓት ኃይሎች ምንም አይነት የባህል፣ የሽምግል እና የህግ የበላይነት መርህ የሌላቸው ናቸው።
ህዝቡ በከባድ መከራና ስቃይ ውስጥ ቆይቷል ያሉት ኮለኔሉ፣ ባለፉት ጊዜያት በመከራ፣ በረሃብ፣ በስደትና በከባድ ስነልቦናዊ ጫና ውስጥ ለማለፍ መገደዱን ገልጸዋል።
አክለውም፣ የህወሓት ኃይሎች ዋነኛ ትኩረት ህዝቡን ማገልገል ሳይሆን ሀብትና ገንዘብ መሰብሰብ መሆኑን ገልጸዋል።
እነዚህ አካላት ህልውናቸውን ማስቀጠል የሚችሉት በትግራይ ውስጥ ሁከት፣ ብጥብጥና አለመረጋጋት ሲኖር ብቻ እንደሆነና ሰላም የማይፈልጉ መሆናቸውንም አብራርተዋል።
በ- ታደለ ገበየሁ












