
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር የሆኑት ትዕዛዙ መሐመድ በ “NBC ዓለም-አቀፍ” ፕሮግራም ላይ ቀርበው በቀጣናው ጂኦፖለቲካ ዙሪያ ሰፊ ትንታኔ ሰጥተዋል። በቆይታቸውም የእስራኤል ምርጫ፣ የቀይ ባህር ጸጥታ እና የአባይ ወንዝ ውዝግብ የቀጣናውን የወደፊት እጣ ፈንታ እንደሚወስኑ በዝርዝር አብራርተዋል።
መምህሩ እንደገለፁት፤ የእስራኤል ምርጫ የመካከለኛውን ምስራቅ የፖለቲካ ሁኔታ የሚወስን በመሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ጉጉት የሚጠበቅ ነው። በቤንያሚን ኔታንያሁ የሚመራው ወታደራዊ እርምጃ በህዝቡ ዘንድ የሚገመገምበት ትልቅ ሁነት መሆኑንም አንስተዋል።
በተጨማሪም ምርጫው ከወትሮው በተለየ ከፍተኛ የህዝብ ተሳትፎ የታየበት እንዲሁም የአሜሪካንና የዓለምን ፖለቲካ አቅጣጫ ጭምር የሚቀይር እንደሆነ አመልክተዋል።
በግብፅ ዋና ተዋናይነት ስለተፈረመው የ«አል-አለሜን» (ግብጽ፣ ሱዳን፣ ሶማሊያ እና ኤርትራ የተስማሙት)ስምምነት ያነሱ ሲሆን፣ ዋና ዓላማው በቀይ ባህር ጸጥታ ስም ኢትዮጵያን ማግለል መሆኑንም አስረድተዋል። ግብፅ ለኤርትራ ሉዓላዊነት እቆማለሁ የምትለው ኢትዮጵያን በወደብ ክፍያ በማዳከም በአባይ ወንዝ ላይ እንዳታለማ ለማድረግ የጠነሰሰችው ሴራ እንደሆነም አጋልጠዋል።
መምህር ትዕዛዙ አክለውም፣ ኢትዮጵያ የባህር በር ስትነፈግ የተሰራውን ታሪካዊ ስህተት የሚያርም ትውልድ መምጣቱን ገልጸዋል።

የግብፅ ውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ምክንያታዊ እንዳልሆነ በማንሳት፣ ካይሮ ሳውዲ አረቢያን በወታደራዊ መንገድ ለመደገፍ መወሰኗ ከሁቲዎችና ከኢራን ጋር ቀጥተኛ ግጭት ውስጥ ስለሚከታት የራሷን የስዊዝ ካናል ገቢ አደጋ ላይ የሚጥል የተሳሳተ ስሌት ነው የተጠቀመችው ብለዋል። በአንጻሩ በቴሄራን የተደረገው የሳውዲና የኢራን ባለስልጣናት መግባባት የውጭ ጣልቃ ገብነትን አስቀርቶ ሰላም ለማምጣት ትልቅ ፋይዳ አለው ነው ያሉት።
ስለ አባይ ወንዝ ውዝግብ መምህር ትዕዛዙ ሲያብራሩ፣ ካይሮ “ዓለም አቀፍ ህግ ‘ጉዳት አለማድረስ’ (No harm)” በሚል የምታቀርበው መከራከሪያ የተሳሳተ ትርጉም መሆኑን አስታውሰው፣ ትክክለኛው ዓለም አቀፍ ህግ ‘ጉልህ ጉዳት አለማድረስ’ (NO significant harm) የሚል መሆኑን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ህግን ባከበረ መልኩ በገዛ ወንዞቿ ላይ የማልማትና የመጠቀም መብቷን በጽናት ማስቀጠል እንዳለባትም ተናግረዋል።
በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለውን ውጥረትን በተመለከተም፣ የሩሲያ መንግስት ጉዳዩን ለማስታረቅና ለማደራደር ያሳየው ዝግጁነት የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር ሁሉንም ዲፕሎማሲያዊ መንገዶች ልትጠቀም እንደሚገባም ነው የገለጹት።
የቀጣናውን አሁናዊ ሁኔታ በNBC ዓለም አቀፍ ያብራሩት የዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ ሌሎች ዓለማቀፋዊ ጉዳዮችንም ዳስሰዋል።
በ-በረከት አስረስ












