
በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው የ“ብርጌድ ንሃመዱ” የኤርትራ ተቃዋሚ ከፍተኛ አመራሮች፣ በኤርትራ የነበረው የፍርሃት ግንብ ሙሉ በሙሉ መሰበሩንና ስርዓቱ ህዝባዊ መሰረት አጥቶ ራቁቱን መቅረቱን በይፋ ተናግረዋል።
አመራሮቹ ሀገሪቱ ያለችበትን አስከፊ ሁኔታ ሲያስረዱ፣ በአሁኑ ወቅት ኤርትራ ማለት ምንም አይነት መስኮትና በር የሌላት፣ አራት በአራት የሆነች ትልቅ እስር ቤት መሆኗን ገልጸዋል።
አክለውም በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኤርትራውያን “2 ፐርሰንት” የተባለውን ታክስ ካልከፈሉ በስተቀር በሀገር ውስጥ ያሉ ቤተሰቦቻቸው ምንም አይነት ማህበራዊ አገልግሎቶችን ማግኘት እንደማይችሉ አመራሮቹ ገልጸዋል። ወጣቱ ይህንን የኢኮኖሚ ጭቆና በቃኝ በማለት ሥርዓቱን በጽኑ እየተቃወመው ይገኛሉ ነው ያሉት።


የሻዕቢያ አገዛዝ የፈጠረውን የተሳሳተ ትርክት ሲያስረዱም፣ “እኛ ስናድግ ኢትዮጵያ የእኛ ጠላት ናት፣ ገዳይ ናት ተብለን ነው ያደግነው፤ አሁን ግን ከዚህ ሥርዓት በላይ ኢትዮጵያ እንደምትሻል አምነናል” ብለዋል። ለዚህም ማሳያ የኤርትራ ወጣቶች ከ 2 ሺህ እስከ 5 ሺህ ዶላር እየከፈሉ ድንበር በመሻገር ወደ ኢትዮጵያ በስፋት እየገቡ እንደሆነ ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት የኤርትራ ሰራዊትም ጭምር ሥርዓቱን ለመክዳት እድል እየጠበቀ ሲሆን፣ ክፍተት ባገኘ ቅጽበት በቀጥታ ወደ ኢትዮጵያ መከላከያ ለመቀላቀል ሙሉ በሙሉ ዝግጁነት ላይ መሆኑንም ተናግሯል።
የእነዚህ ከፍተኛ አመራሮች ሙሉ ቆይታና ያልተሰሙ ወቅታዊ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች በስፋት ቀርበዋል። ይህን የጊዜ ግስ መሰናዶ ዛሬ ምሽት 2፡30 ላይ በNBC ኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ማሕበራዊ ሚዲያ አማራጮች ይቀርባል።
በ-በረከት አስረስ












