በይሮፓ ሊግ ምሽት ላይ ተጠባቂ ጨዋታዎች ይከናወናሉ።
በሁለተኛ ዙር 18 ጨዋታዎች ከምሽት 1 ሰዓት 45 ጀምሮ በተለያዩ ስታዲየሞች የሚከናወኑ ይሆናል። ምሽት 4 ሰዓት የእንግሊዙ ኖቲንግሃም ፎረስት በሜዳው ሲቲ ግራውንድ የዴንማርኩን ሚቺላንድን ያስተናግዳል።
በደካማ የውጤት ጉዞ ላይ የሚገኘው ፎረስት በሁሉም ውድድሮች ባደረጋቸው ባለፉት አምስት ጨዋታዎች አንዱንም ማሸነፍ ተስኖታል። አዲሱ አሰልጣኝ አንጅ ፖስትኮግሉ ከመጡ በኋላ ደካማ አጀማመር ላይ ሲሆኑ፣ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ወደ ሜዳ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በመጀመሪያ ጨዋታቸው ፎረስት ወደ ስፔን አቅንቶ ከሪያል ቤቲስ አቻ ሲለያይ፣ሚቺላንድም ወደ ስፔን ተጉዞ በሪያል ሶሲየዳድ ተሸንፏል። ሌላኛው የእንግሊዙ ቡድን አስቶን ቪላ በተመሳሳይ ምሽት 4 ሰዓት ወደ ኔዘርላንድ አቅንቶ ፌይኖርድን ይገጥማል።
የአሰልጣኝ ኡናይ ኢምሬ ቪላ እንደ ፎረስት ሁሉ ደካማ የውድድር አመት ያደረገ ሲሆን፤ ባሳለፍነው ቅዳሜ የመጀመሪያ የፕሪምየር ሊግ ድሉ አሳክቶ መነቃቃት ችሏል። ሁለቱ ቡድኖች በመድረኩ ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ ቪላ ቦሎኛን ሲያሸንፍ፤ ፌይኖርድ በስፖርቲንግ ብራጋ ተሸንፏል።
በምሽቱ ተጠባቂ ጨዋታ በቪላ በኩል ጆን ማጊን፣ታይረን ሚንግስ፣ ዮሪ ቴሌማንስ እና አማዱ ኦናና በጉዳት ሳቢያ ከቡድን ስብስብ ውጪ ተደርገዋል። በሌሎች ስታዲየሞች ሮማ ከሊል፣ፖርቶ ከክሬቭና ዝቬዝዳ፣ ሊዮን ከሳልዝበርግ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።
በ – አልፈሪድ ነስሮ












