በአዲስ አበባ ቅዳሜ መስከረም 24 ቀን 2018 ዓ.ም በሚከበረው የኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ በዓል ምክንያት ለተሽከርካሪዎችና ለእግረኞች ዝግ የሚሆኑ መንገዶችን የከተማዋ ፖሊስ ይፋ አድርጓል፡፡
የኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ በዓል ተከብሮ እስከሚጠናቀቅ፦
፨ ከሜክሲኮ አደባባይ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው ሜክሲኮ፣
፨ ከወሎ ሠፈር መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ኦሎምፒያ፣
፨ ከቄራ ሜክሲኮ የሚወስደው መንገድ ቡልጋሪያ፣
፨ ከመርካቶ በአቡነ ተ/ኃይማኖት ወደ ጥቁር አንበሳ የሚወስደው መንገድ አቡነ ተክለኃይማኖት ቤተክርስቲያን፣
፨ ከቅዱስ ኡራኤል አደባባይ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ቅዱስ ኡራኤል አደባባይ፣
፨ ከቦሌ አቅጣጫ ወደ መስቀል አደባባይ ለሚመጡ ተሽከርካሪዎች ኦሎምፒያ አደባባይ ላይና ታች እንዲሁም ግራና ቀኝ፣
፨ ከመስቀል ፍላወር ወደ ኦሎምፒያ የሚወስደው መንገድ ጋዜቦ አደባባይ፣
፨ ከአጎና ሲኒማ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ጥላሁን አደባባይ (አራተኛ ክፍለ ጦር)፣
፨ ከለገሀር መብራት ወደ መስቀል አደባባይ ለገሀር መብራት፣
፨ ከቴሌ ማቋረጫ ወደ ስታድዮም ለሚጓዙ ቴሌ ማቋረጫ፣
፨ ከራስ ሆቴል ወደ ስታድየም ለሚመጡ ተሽከርካሪዎች ራስ ሆቴል፣
፨ ከሐራምቤ መብራት ወይም ከአምባሳደር ሲኒማ ወደ መስቀል አደባባይ ሃራምቤ መብራት፣
፨ ከአዲሱ ገበያ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ባንኮዲሮማ፣
፨ ከብሔራዊ ቤተ መንግስት ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ብሔራዊ ቤተ መንግስት አጠገብ፣
፨ ከካዛንቺስ ሼል ወደ ባምቢስ የሚወስደው መንገድ ካዛንቺስ ሼል አጠገብ እንዲሁም
፨ ከጁፒተር ሆቴል ወደ ኢሲኤየሚወስደው መንገድ ባምቢስ ሳልኮት ህንፃ አጠገብ
ከመስከረም 23 ቀን 2018 ዓ.ም ከቀኑ 6 ሰዓት ጀምሮ ፕሮግራሙ እስከሚጠናቀቅ ድረስ መንገዶቹ ለተሽከርካሪ ዝግ እንደሚሆኑ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታውቋል፡፡
በአዲስ አበባ ዙሪያ ከሚገኙ የሸገር ከተማ አካባቢዎች በርካታ ህዝብ በዓሉን ለማክበር ከዋዜማው ጀምሮ ወደ ከተማው የሚገባ በመሆኑ መላው ህብረተሰብ ተገቢውን አክብሮት በመስጠት የእንግዳ ተቀባይነት እሴታችንን አጉልቶ ሊያሳይ እንደሚገባ ፖሊስ አስታውሶ በዓሉ በሚከበርበት ዙሪያ እና በአካባቢው በግራና በቀኝ ለረጅምም ሆነ ለአጭር ጊዜ ተሽከርካሪ አቁሞ መሄድ ፍፁም የተከለከለ መሆኑን ገልጿል፡፡
በዓሉ በሠላም እንዲከበር የፀጥታ አካላት ትኩረት ሰጥተው ወደ ተግባር በመግባት እየሰሩ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልጾ በተለይ በዓሉ ወደሚከበርበት ስፍራ የሚመጡ ታዳሚዎች ለጋራ ደህንነት ሲባል ፍተሻ መኖሩን ተገንዝበው አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ አሳስቧል።
ከዚህ ቀደም የተከበሩ ኃይማኖታዊና ብሔራዊ በዓላት በሠላም እንዲከበሩ ህብረተሰቡ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በመተባበር ወሳኝ ስራ ማከናወኑን የገለጸው ፖሊስ የዘንድሮው የኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ በዓል በሠላም እንዲከበር የበዓሉ ታዳሚዎች እና የከተማው ነዋሪ የተለመደውን ትብብር እንዲያደርጉ በፀጥታ አካላት ስም ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
ህብረተሰቡ ለፀጥታ ስጋት የሆኑ አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙት በ011-1-26-43-59 ፣ 011-5-52-63-02/03፣ 011-5-52-40-77፣ 011-5-54-36-78 እና 011-5-54-36-81 እንዲሁም በ987፣ 991 እና 816 ነፃ የስልክ መስመሮች ጥቆማ በመስጠትና አስፈላጊውን ትብብር በማድረግ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጠቅላይ መምሪያ ጥሪ አቅርቧል።












