በጣና ሀይቅ ላይ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ተገዝታ ወደሀገር ውስጥ የገባችውና የተለያዩ ከተሞች አቋርጣ አገልግሎት ወደምትሰጥበት የጣና ሀይቅ እየተጓጓዘች ያለችው ጣናነሽ ሁለት ጀልባ የዓባይን በረሀ እያቋረጠች ትገኛለች።
ብዙ ኪሎሜትር በየብስ ላይ ተጉዛ እንድትሄድ መደረጉን በማስመልከት የተነሱ የአዋጭነትና አንዳንድ ጥያቄዎችን በተመለከተ የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ደምሰው በንቲን ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በቅድሚያ የጀልባዋን አካላት ለትራንስፖርት በሚመች መልኩ ለያይቶ በማምጣት በሀገር ውስጥ መገጣጠም አለመቻሉን አስመልክተው ሲናገሩ፣ እንደነዚህ አይነት ትላልቅ የጀልባ አካላትን መገጣጠም የሚችል በሙያው የሰለጠነ የሰው ሀይል ባለመኖሩ ጠቅሰው፣ የደኅንነት ችግር እንዳይገጥም ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ስለሚገባ በመኪና ማጓጓዙ ተመራጭ መሆኑን ተናግረዋል።
እንዲህ ያለው ተሞክሮ በመሬት በተከበቡ ሌሎች ሀገራትም ትላልቅ ጀልባዎችን ዲዛይን አድርገው ከሰሯቸውና በሙያው ልዩ ስልጠና ከሌላቸው ባለሙያዎች ውጭ ዳግም ለመገጣጠም በሚሞከርበት ወቅት ከጀልባዎቹ ውስብስብ አሰራር አኳያ ትልቅ ብልሽት ያጋጥማል ነው ያሉት።
አቶ ደምስ አያይዘውም፣ የጀልባ አካላትን ለያይቶ ማምጣትና ገጣጥሞ በጥቅም ላይ ማዋል የአገልግሎት ዘመናቸውን ከማሳጠርም ባለፈ ለትልቅ አደጋና ብልሽት የሚዳርግ እንደሆነ ገልፀዋል።
እንደ ስዊዘርላንድ ባሉ የሰለጠኑ ሀገሮችም ትላልቅ የትራንስፖርትና የቱሪስት ጀልባዎችን ክፍሎች ለያይቶ ከማምጣት ይልቅ በየብስ ትራንስፖርት አጓጉዘው አገልግሎት ወደሚሰጡበት የውሀ አካል መውሰድ ተመራጭ እንደሆነ ተናግረዋል።
ይህም ሲሆን ከረጅም ጊዜ አገልግሎት አኳያ፣ ከፍተኛ የዘርፉ አማካሪዎች ለረጅም ጊዜ የአዋጭነት ጥናት ተደርጎ እና ከዓለም አቀፍ ተሞክሮ አንጻር ጀልባዋ በየብስ ተጓጉዛ ወደሚፈለገው ቦታ እንድትደርስ መወሰኑን ገልፀዋል።
በቀጣይ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በሚያካልላቸው የውሀ ክፍሎች፣ በባሮ ወንዝ ላይ ተመሳሳይ አገልግሎት የሚሰጡ አነስተኛ ጀልባዎችን ለማሰማራት መታቀዱን ተናግረዋል።
ይህንንም በስፋት ለማድረግ እንዲቻል ቀላል ጀልባዎችን በሀገር ውስጥ ለመገጣጠም የሚያስችል ማዕከል እንደሚከፈትና ባለሙያዎችንም ከሀገር ውጭ አሰልጥኖ በማምጣት በዘርፉ እንዲሰማሩ ለማድረግ መታቀዱን ነው የጠቆሙት።
ይህ እስኪሆን ድረስ ግን በተለይ እንደጣናነሽ አይነት ዘመናዊ እና ግዙፍ ጀልባዎችን ለማጓጓዝ ያለው አማራጭ በየብስ አሁን እየተደረገ እንዳለው መሆኑ የጠቆሙት አቶ ደምስ፣ ወደፊት ግን በዚህ ዘርፍ ያለውን የሀገር ውስጥ አቅም ለማሻሻልና ለማሳደግ እንደታሰበ ገልፀውልናል።
ጣናነሽ ሁለት በሀገራችን እስከዛሬ ካሉት የትራንስፖርትና የቱሪስት ጀልባዎች በላቀ ሁኔታ እጅግ ዘመናዊ እና ግዙፍ ጀልባ መሆኗ ይታወቃል።












