፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ጳጉሜ 05 2016| NBC ETHIOPIA- ጳጉሜ 5 የነገ ቀን ”የዛሬ ትጋት፤ ለነገ ትሩፋት” በሚል መሪ መልዕክት በባሕር ዳር ከተማ በተለያዩ ሥነ ሥርዓቶች እየተከበረ ነው።
በአከባበር ሥነ ሥርዓቱ የብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር)፣ የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍስሐ ደሳለኝ፣ እና የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማውን ጨምሮ የክልል እና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ መሪዎች ተገኝተዋል።
የአማራ ክልል ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ብርቱካን ሲሳይ በሥነ ሥርዓቱ ላይ አዲሱ ዓመት ሴቶች፣ ሕጻናት፣ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች በሰላም የሚኖሩበት እንዲኾን መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።

የነገ ትውልድ ተረካቢ ሕጻናት እና ሀገር ያቆዩን አረጋውያንም ክብር ሊሰጣቸው እና እንክብካቤ ሊደረግላቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ “ዛሬ ሠርተን መልካም ውጤት ስናመጣ የቀጣዩን ትውልድ እጣ ፈንታ እንወስናለን” ብለዋል።
እስካሁንም በብዙ ውጣ ውረድ አልፈናል፤ ለትውልድ የሚጠቅም በጎ እርሾ እንዳበጀን ሁሉ ለትውልድ የማይጠቅም መጥፎ ነገርም ተሠርቷል ብለዋል። በቀጣይም ስህተቱን አርመን በጎውን አጠናክረን በመቀጠል ለትውልድ መልካም ነገር ማቆየት አለብን ነው ያሉት።

እጣ ፈንታቸው በኛ ላይ ለተመሠረቱ ሕጻናት እና ወጣቶች ከኛ የሚጠበቅ ነገር አለ ያሉት አቶ ይርጋ ሰላም እና ነጻነት ይፈልጋሉ፤ ሰላማችን አስከብረን በሰላም የሚኖሩበት ሀገር እና ክልል መፍጠር አለብንም ብለዋል።
ታሪክ ቅርስ እና ባሕልን ጠብቆ ለትውልድ ለማስረከብ ብዙ እንደሚጠበቅም አስገንዝበዋል። አንድነትን መሠረት አድርጎ ታሪክ የተሠራበትን ኅብረ ብሔራዊነት ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባም አብራርተዋል።
ሕጻናትን በመቅረጽ እና በመገንባት ለነገ የሚኾን ቅርስ ለመፍጠር ማስተማር እንደሚገባም አቶ ይርጋ አሳስበዋል።ለነገ እናስብ፣ እናቅድ፣ ሀገርን እንጠብቅ፣ ለነገ እንሥራ ያሉት አቶ ይርጋ መጭው ዓመት የሰላም፣ የመነጋገር እና የመተባበር እንዲሆን ተመኝተዋል።
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Facebook -https://www.facebook.com/ethiopiannbc
Telegram-https://t.me/nbcethiopiatv












