፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ጳጉሜ 05 2016| NBC ETHIOPIA- ጳጉሜን 05 የነገ ቀን – ”የዛሬ ትጋት፤ ለነገ ትሩፋት” በሚል መሪ ቃል በባሕር ዳር ከተማ እየተከበረ ነው።
የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) እና የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማውን ጨምሮ ሌሎች የከተማው እና የክልል የሥራ ኀላፊዎች በበዓሉ ላይ ተገኝተዋል።
በሥነ ሥርዓቱ የማርሽ ባንድ፣ የሰርከስ ትርዒት፣ የኪነት፣ እና የጎዳና ላይ ትርኢቶች እየተካሄዱ ነው።
የሥነ ሥርዓቱን ማስጀመሪያ ንግግር ያደረጉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው የጳጉሜ ቀናትን በተለያዩ የሰላም፣ የልማት እና የፍቅር መልዕክቶች ሲከበሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
ዛሬ ላይ ኾነን የምንሠራው ለነገው ቀን ትልቅ አዎንታዊ ተጽዕኖ አለው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ባለፈው ዓመት የሰላም እጦት ገጥሞን እንደነበርም አስታውሰዋል። በቀጣዩ ዓመት ሁላችንም በአንድነት ስለ ሀገራችን የምንሠራበት የምንመካከርበት ኹኔታ እንዲፈጠር ታስቦ የሚከበር በዓል ነው ብለዋል የዛሬውን በዓል።
ሁላችንም ስለ ሰላም እና ስለ ፍቅር የምንነጋገርበት፣ በመመካከር የምንሠራበት፣ የጥይት ድምጽ የማንሰማበት እንዲኾን እና በሰላም ሠርተን ልጆቻችንን የምናሳድግበት እና ከተማችንን የምናለማበት መኾን አለበትም ብለዋል።
ጦርነት ችግርን አይፈታም። “ካለፈው አንድ ዓመት ተምረን ቀጣዩን ዓመት የአማራ ክልል ሕዝብን ችግር የምንፈታበት ማድረግ አለብን” ብለዋል። የከተማው ሕዝብም ለሰላሙ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተስፋ አደርጋለሁ ነው ያሉት። ኅብረተሰቡ እና የፀጥታ ኃይሉም ለሰላም ላበረከቱት አስተዋጽኦ አመስግነዋል።
የጳጉሜን ቀናት በተለያዩ ሁነቶች ሲከበሩ ተሳትፎ ያደረጉ እና አስተዋጽኦ ያበረከቱ አካላትንም አመስግነዋል ዘገባው የአሚኮ ነው፡፡
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Facebook -https://www.facebook.com/ethiopiannbc
Telegram-https://t.me/nbcethiopiatv












