አዲስ አበባ | ህዳር 07 2016| NBC ETHIOPIA -የትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ጁሊ ምህረቱ የስዕል ሥራ ዳግም የአፍሪካን የጥበብ ሥራ ክብረ ወሰን በመስበር በጨረታ በትልቅ ዋጋ የተሸጠላት አፍሪካዊት አርቲስት ሆናለች።

የ52 ዓመቷ ጁሊ የተወለደችው በኢትዮጵያ ሲሆን በፖለቲካዊ ምክንያት በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ ከቤተሰቧ ጋር ወደ አሜሪካ አምርታለች፡፡
ጁሊ ምህረቱ ትልቅ ዕድገት እያሳየ ባለው ዘመናዊ የአፍሪካ የሥነ-ጥበብ ሥራ ላይ ከፍተኛ ዝናን ካፈሩ ሰዓሊያን መካከል አንዷ ነች።
የሳዕሊዋ ዎከርስ ዊዝ ዘ ዶውን ኤንድ ሞርኒንግ የተሰኘው ስራ በኒውዮርክ በተካሄደ ጨረታ በ10.7 ሚሊዮን ዶላር ተሽጧል። ይሄን ስዕል ለመሳል እንደ መንስኤ የሆናት እ.ኤ.አ 2005 ላይ ሄሪኬን ካትሪና የተባለው አውሎ ንፋስ ኒው ኦርሊያንስ ከተማ ላይ ያደረሰውን ጉዳት ተከትሎ በተዘጋጀው ዐውደ ርዕይ ላይ ነበር።
ይህ በሸራ ላይ የተሳለ የጥበብ ሥራ ስያሜውን ያገኘው ላንግስተን ሂዩስ እ.ኤ አ በ1920 ካሳተመው ግጥም ነው።
ስዕሉን ለመግዛት ሁለት ተጫራቾች እየተፎካከሩ ዋጋ በከፍተኛ መጠን ጨምሮ 9.5 ሚሊዮን ዶላር የደረሰ ሲሆን ሌሎች ክፍያዎች ተጨማምረው አጠቃላይ ዋጋው 10.7 ሚሊዮን ዶላር ሆኗል።

ጁሊ ምህረቱ በተመሳሳይ የሥዕል ሥራዋ በከፍተኛ ክፍያ በመሸጡ ቀደም ሲልም የአፍሪካ አሜሪካዊ አርቲስት ክብረ ወሰንን የያዘ ነበር።
ይህ የጁሊ የሥዕል ሥራ በዚህ ያህል ከፍተኛ ገንዘብ ለሽያጭ መብቃቱ በገበያ ላይ ተፈላጊነቱ እየጨመረ ላለው ለወቅታዊው የአፍሪካውያን የአብስትራክት ስዕል የጥበብ ሥራ ጠንካራ ፍላጎት መኖሩን አመላካች ነው ተብሏል።
ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ጁሊ ምህረቱ በጥበብ ሥራዎቿ በአውሮፓ እና በአሜሪካ ከፍ ያለ ዕውቅናን ያገኘች አርቲስት ስትሆን ሥራዎቿንም በተለያዩ ታላላቅ ኤግዚቢሽኖች ስታሳይ ቆይታለች።
ባለፈው ዓመት አጋማሽ ላይ የጀርመኑ ታዋቂ የመኪና አምራች ኩባንያ ቢኤምደብሊው ለሕዝብ ዕይታ የሚቀርበውን ተሽከርካሪውን በጥበብ ሥራዋ እንድታስውብለት መርጧታል።
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Facebook – https://www.facebook.com/ethiopiannbc
Telegram-https://t.me/nbcethiopiatv
#NBC_ETHIOPIA
#ሆኖ_መገኘት












