
ከሃያ አምስት ዓመታት በፊት፣ ልክ በዛሬዋ ዕለት ማለትም ህዳር 16 ቀን 1994 ዓ.ም አዲስ አበባ የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ ታላቁ ሩጫን “ለሕይወትህ ዋጋ ስጥ” በሚል መሪ ቃል ማስተናገድ ጀመረች። ይህ ዕለት በሀገራችን የአትሌቲክስና የአካታች ስፖርት ታሪክ ውስጥ የማይረሳና የመጀመሪያ ምዕራፍ ሆኖ ይታወሳል። በኢትዮጵያውያን መካከል አንድነትን፣ ጤናማ እንቅስቃሴንና የሩጫ ባህልን ለማስረጽ የተጀመረው ይህ ጉዞ ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ የብዙዎችን ቀልብ የሳበ ታላቅ ክስተት ሆኖ ቀጥሏል።
ለሕይወትህ ዋጋ ስጥ” የሚለው መሪ ቃል የኢትዮጵያ ህዝብ ሩጫን ከቀላል የአካል ብቃት እንቅስቃሴና የውድድር መንፈስ በላይ ከፍ አድርጎ፣እንዲመለከትና በወቅቱ በሀገሪቱ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ይስፋፋ የነበረውን የኤችአይቪ ኤድስ ወረርሽኝ ለመከላከል እንዲሁም በኅብረተሰቡ ውስጥ ግንዛቤ ለመፍጠር ነበር።
በዚያ ታሪካዊ ዕለት የውድድሩ መስራች የሆነው አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴና ሌሎች ታዋቂ አትሌቶችን ጨምሮ ወደ 10 ሺህ የሚጠጉ ተሳታፊዎች በ10 ኪሎ ሜትር የሩጫ መስመር ላይ በመሰለፍ የዚህን ታላቅ የስፖርት በዓል ጠንካራ መሠረት ጥለዋል። ተወዳዳሪዎችና ተሳታፊዎች የአዲስ አበባን ጎዳናዎች ያጥለቀለቁበት ትዕይንት ፤ስፖርት ሰዎችን የማቀራረብና የጋራ መንፈስ የመፍጠር ኃይሉ ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆነ በግልጽ አሳይቷል። ያ የመጀመሪያ እርምጃ በቀላሉ የሚያልፍ ውድድር ሳይሆን፣ ለቀጣዮቹ ዓመታት የሚዘልቅ ታላቅ የስፖርት ባህል ጅማሬ ነበር።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በሩጫ ስፖርት የምትታወቀው ኢትዮጵያ፣ ይህንን ውድድር ወደ ባህላዊና ማኅበራዊ በዓልነት በማሳደግ የራሷን መገለጫ ከማስቀመጥ ባለፈ ። በየአመቱ የሚካሄድ የጤና እና የአብሮነት ኩራት መግለጫ ሆኖ ዘልቋል።
ይህ ዕለት የሩጫ ውድድር የተካሄደበት ብቻ ሳይሆን፣ በኢትዮጵያ የስፖርት ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የተከፈተበትም ታላቅ ቀን ነው። የአካታች ሩጫን በማስፋፋት ሰፊው ሕዝብ በስፖርቱ እንዲሳተፍና ከአትሌቲክስ ባህል ጋር ይበልጥ እንዲተሳሰር የከፈተው በር ዛሬም ድረስ ትርጉሙ አልተቀየረም። የመጀመሪያው ሩጫ የፈጠረው መነሳሳት የሀገሪቱን የስፖርት እንቅስቃሴ ወደ አዲስ ከፍታ ለማሸጋገር ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
ዛሬ ከ25 ዓመታት በኋላ ታሪክን ስናስታውስ፣ ህዳር 16 ቀን 1994 ዓ.ም. የተጀመረው ጉዞ ምን ያህል ፍሬ እንዳፈራና ባህል ሆኖ እንደጸና እናያለን። የመጀመሪያዎቹ 10 ሺህ ተሳታፊዎች የዘሩት ዘር በኢትዮጵያ የአትሌቲክስና የስፖርት ታሪክ ውስጥ ዘላለማዊ አሻራ ትቷል። በዚህም ምክንያት ይህ ዕለት የታላቁን ሩጫ መነሻ ብቻ ሳይሆን፣ የአገራችንን የስፖርት ባህል ያደመቀ ታሪካዊ ቀን ሆኖ ቀጥሏል።
በ -ታደለ ገበየሁ










