በዓለም ላይ አሜሪካ፣ ሩሲያና ቻይና በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በወታደራዊ ተጽዕኖ ለመበላለጥ ጥረት በሚያደርጉበት በዚህ ወቅት ፣ የሶስቱ ሀገራት መሪዎች በአንድ መድረክ ላይ መገናኘታቸው የዓለምን ቀጣይ የፖለቲካና የኢኮኖሚ አቅጣጫ በተመለከተ ትልቅ ጥያቄ አስነስቷል።

መሪዎች በቻይና ሼንዘን በሚካሄደው የኤዥያ-ፓሲፊክ ኢኮኖሚ ትብብር (APEC) መድረክ ላይ መገናኘታቸው ከኢኮኖሚ ትብብር ባለፈ ዓለም ወደ አዲስ የኃይል ሚዛን እየተሸጋገረች መሆኗን የሚያመለክት እንደሆነ ተገልጿል።
የኤዥያ-ፓሲፊክ ኢኮኖሚ ትብብር 21 አባል ሀገራትን ያቀፈ ትልቅ የኢኮኖሚ ትብብር መድረክ ሲሆን፣ የመሪዎች በዚህ መድረክ መገናኘት በዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ላይ ሰፊ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ተነስቷል። በተለይም ሺ ጅንፒንግና ቭላድሚር ፑቲን ከትራምፕ ጋር ከመገናኘታቸው በፊት በመነጋገር የኢራንን፣ የዩክሬንንና የዓለም አጠቃላይ ሁኔታ መወያየታቸው የሞስኮና የቤጂንግን የጋራ አቋም የሚያሳይ መሆኑ ተነግሯል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፉ ግንኙነት መምህር እንዲሁም በNBC ኢትዮጵያ የ“ዓለም አቀፍ” ፕሮግራም ተባባሪ አዘጋጅ የሆኑት ትዕዛዙ መሐመድ፣ ሩሲያና ቻይና በአንድ ኃያል ሀገር የሚመራውን የዓለም ሥርዓት በመቀየር ብዝሃ ዋልታ ያለው የዓለም ሥርዓት እንዲፈጠር እየጣሩ መሆኑን አብራርተዋል። ይህም የምዕራቡ ዓለም ብቻውን የሚመራበት የኃይል ሚዛን እየተለወጠ መምጣቱን እንደሚያመለክት ገልጸዋል።
መምህር ትዕዛዙ እንዳብራሩት፣ ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃትና ከሶቪየት ኅብረት መፍረስ በኋላ አሜሪካና ምዕራባውያን በዓለም ፖለቲካ ላይ የበላይነት እንደነበራቸው አስታውሰው፣ አሁን ግን ሩሲያና ቻይና ይህንን ሁኔታ በመቀየር የባለብዙ ዋልታ(Multipolar) የዓለም ሥርዓት እንዲፈጠር እንደሚፈልጉ አመልክተዋል። ይህም በማደግ ላይ ላሉ እና ለመካከለኛ ኃያላን ሀገራት አዲስ ዕድል ሊፈጥር እንደሚችልም ጠቁመዋል።

እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት ከአንድ ኃያል ሀገር ጋር ብቻ ትብብርን ከማድረግ ይልቅ ከተለያዩ የዓለም ኃይሎች ጋር ግንኙነት መፍጠር ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበርና የውስጥ አቅምን ለማጠናከር የተሻለ አማራጭ መሆኑ ተነግሯል። በተለይም ኢትዮጵያ በባሕር በርና በህዳሴ ግድብ ጉዳዮች ላይ የራሷን ብሔራዊ ጥቅም በማስጠበቅ በዓለም አቀፍ ሂደቶች ላይ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባትም ተጠቁሟል።
የሦስቱ መሪዎች ስብሰባ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሊያበቃ ሲል የሶቭየት ሕብረት መሪ ጆሴፍ ስታሊን፣ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ፍራንክሊን ሩዝቬልት እና የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዊንስተን ቸርችል በያልታ ከተማ ያደረጉትን ታሪካዊ ጉባኤ የሚያስታውስ መሆኑ ተገልጿል።
በያልታና በአሁኑ ጉባኤ መካከል ስላለው ተመሳሳይነት መምህር ትዕዛዙ ሲያስረዱ፣ ዓለም ከትልቅ ቀውስ በኋላ የሚኖራትን አቅጣጫ በመወሰን ረገድ ያላቸው ተፅዕኖ ነው ብለዋል። ሦስቱ ኃያላን ሀገራት በቁልፍ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ላይ ከደረሱ የወደፊቱን ዓለም በመቅረጽ ረገድ ትልቅ ሚና ሊኖራቸው እንደሚችልም አመልክተዋል።

ከዚህ ባለፈ የሦስቱ መሪዎች ውይይት በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ተጨባጭ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል አንስተው፣ በተለይም በዩክሬን ያለው ጦርነት ወደ መፍትሔ ከመጣ የግብርና ምርቶች አቅርቦትና ዋጋ ላይ አዎንታዊ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ተናግረዋል። አክለውም በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው ቀውስ ከተፈታ የነዳጅ ዋጋ መቀነስንና የዓለም አቀፍ የዋጋ ግሽበትን ማረጋጋት እንደሚያስችል አንስተዋል።
በሌላ በኩል የአሜሪካና የቻይና የንግድና የቴክኖሎጂ ፉክክር፣ የሳይበር ደኅንነት ስጋቶችና በአሜሪካ የደኅንነት ተቋማት ውስጥ የሚታዩ የቅንጅት ችግሮች በጉባኤው ላይ ተጽዕኖ ሊኖራቸው እንደሚችል ተባባሪ አዘጋጁ ጠቁመው፣ በማይክሮሶፍት ዙሪያ የሚነሱ የቴክኖሎጂና የሳይበር ደኅንነት ጉዳዮች በሁለቱ ኃያላን መካከል ያለውን ፉክክር የበለጠ ሊያጠናክሩት እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

የጉባኤው ዋና ትኩረት በዩክሬን፣ በኢራን ወይም በኤዥያ-ፓሲፊክ ጉዳዮች ላይ ብቻ ሳይሆን ዓለም ወደፊት በምን ዓይነት ሥርዓት ትመራለች የሚለው ጥያቄ መሆኑንም መምህሩ አብራርተዋል። ሺ ጅንፒንግና ፑቲን በብዙ ጉዳዮች የጋራ አቋም ቢኖራቸውም፣ ትራምፕ ግን የአሜሪካን ብሔራዊ ጥቅም በማስቀደም ወደ ውይይቱ እንደሚቀርቡ አንስተው፣ የሦስቱ መሪዎች መግባባት ለሌሎች ሀገራት የተሻለ የተሳትፎ ዕድል ይፈጥራል ወይስ ሀገራቱ የራሳቸውን ተጽዕኖ ለማስፋት ብቻ ይጠቀሙበታል የሚለው አንገብጋቢ ጉዳይ እንደሚሆን ተናግረዋል።
ተባባሪ አዘጋጁ እንዳመለከቱት፣ የዓለም ሥርዓት ለውጥ ከኃይል ሚዛን ብቻ የሚመጣ ሳይሆን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን፣ ሰው ሠራሽ አስተውሎትን (AI)፣ የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ማሻሻያንና የአየር ንብረት ለውጥን ጨምሮ በበርካታ ዘርፎች ላይ የሚደረግን ትብብርን የሚጠይቅ እንደሆነ አስገንዝበዋል።
የጉባኤው ታሪካዊነትና ተጨባጭ ውጤት የሚለካው በሦስቱ መሪዎች መገናኘት ብቻ ሳይሆን በሚደርሱበት መግባባትና በሚወስዱት ተግባራዊ እርምጃ እንደሆነ ተናግረው፣ የምዕራቡ ዓለም ከ1990ዎቹ ጀምሮ የነበረውን የበላይነት ለማስቀጠል ከሞከሩ ጉባኤው የቻይናንና ሩሲያን የኃይል መለካካት ለማሳየት የሚያገለግል መድረክ ብቻ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።

በዩክሬንና በኢራን ያሉ ቀውሶችን በውይይት ለመፍታት፣ በንግድና በትራንስፖርት ዙሪያ ያሉ እንቅፋቶችን ለማስወገድ እንዲሁም የደኅንነት ጉዳዮችን በጋራ ለመፍታት ተግባራዊ መግባባት ላይ ከተደረሰ፣ ጉባኤው እንደ ያልታ ኮንፈረንስ በዓለም ታሪክ የሚታወስ አስፈላጊ ክስተት ሊሆን እንደሚችል ምልከታቸውን ሰጥተዋል።
በ-በረከት አስረስ










