
የህወሓት አመራሮች ራሳቸው በራሳቸው ውስጣዊ ቅራኔዎች ምክንያት የፈጠሩት ጥምረት ሙሉ በሙሉ መክሸፉን በኤንቢሲ ኢትዮጵያ “ጊዜ ግስ” ፕሮግራም ላይ ቆይታ ያደረጉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ ገልጸዋል።
የህወሓት አመራሮች አብዛኛዎቹ እጅ እንደሚሰጡና የህወሓት ኃይል እንደቀድሞው ተስፋ የሚጣልበት እንዳልሆነ ያብራሩት አቶ ጌታቸው፣ የትግራይን ወጣት ሙሉ በሙሉ ማዳን ባይችሉም የህወሓት አመራሮች ወጥነውት የነበረውን አደገኛ ቀውስ በማክሸፍ ረገድ አስተዋጽኦ በማበርከታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በወቅታዊው የጸጥታ ሁኔታ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ ጌታቸው፣ የመከላከያ ሠራዊቱ የዲሲፕሊን አጠባበቅ ላይ ጠንካራ መሆኑንና ወጣቶች ከመከላከያ አባላት ጋር በሰላም እየተቀራረቡ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ሆኖም አንዳንድ የቀሩ የህወሓት አመራሮችና ታጣቂዎች ድንበር አካባቢ ተበታትነው አሁንም ያልተገቡ እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ እንደሚሞክሩ ጠቁመው፣ ይሁን እንጂ የህወሓት ኃይል እንደ አዲስ ተመልሶ ይመጣል ብሎ የሚጠብቅ አካል እንደሌለ አጽንኦት ሰጥተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ ሲናገሩ የኤርትራ መሪዎች የራሳቸውን ሀገር ከሀገርነት ወደ ተራ አቧራነት ከቀየሩ በኋላ፣ ለልማት ማዋል የሚገባቸውን ገንዘብ ለጎረቤት ሀገራት ማተራመስ አጀንዳ ማዋላቸው ከፍተኛ ስህተት መሆኑን አመልክተዋል።
የኤርትራ መንግሥት ከስህተት የመማር አቅሙ እጅግ ዝቅተኛ መሆኑን የገለጹት አቶ ጌታቸው፣ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የፈጸሟቸው ስልታዊ ስህተቶች ሀገሪቱን ከባድ አደጋ ውስጥ እንደሚከቷት አስጠንቅቀዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሰላምን ለማስፈን በሚያደርገው እንቅስቃሴ ኤርትራ እንቅፋት መሆን እንደማይገባት አሳስበው፤ እንቅፋት በሆነች ዕለት ግን ተያይዛ የምትጠፋበት ዕድል ሰፊ መሆኑን ተናግረዋል።
ኤርትራ የምትለኩሰውን እሳት ብቻዋን የምትሞቅበትና የምትቃጠልበት እንጂ አንዳችም ዓለም አቀፍ ኃይል ሊደርስላት እንደማይችልም አስገንዝበዋል።
አቶ ጌታቸው በኤንቢሲ ኢትዮጵያ ጊዜ ግስ መርሀግብር ያደረጉትን ቆይታ በቴሌቪዥን እና በማኅበራዊ ሚዲያ አማራጮቻችን ነገ ቅዳሜ ምሽት ይጠብቁን።
በ- ታደለ ገበየሁ












