
የቀድሞው የአውሮፓ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር አሌክሳንደር ሮንዶስ በሚድል ኢስት አይ ቀርበው በሰጡት ማብራሪያ፣ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ከዓለም አቀፍ የውሃ አጠቃቀም መብቶችና ከኢኮኖሚ ዕድገት አንፃር ወቅታዊና ትክክለኛ መሆኑን አብራርተዋል።
እንደ አንባሳደሩ ገለፃ ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት ከባህር በር ተነጥላ የቆየችበት መንገድ ተገቢ አለመሆኑን በመጥቀስ፣ አገሪቱ በቀይ ባህር ጉዳይ ላይ የምታነሳቸው ጥያቄዎች ሕጋዊና ታሪካዊ አግባብነት እንዳላቸው አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የምታስመዘግበውን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስቀጠል፣ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ስጋቶችን ለመቆጣጠርና በቀጣይነት ለመሻገር በቀይ ባህር በኩል የማለፍ ፍላጎቷ መሠረታዊ መሆኑም ተመልክቷል።

በሌላ በኩል፣ በቀጣናው የሚታዩ የኃይል ሚዛን መዛባትና አለመግባባቶች በአፍሪካ ቀንድ ሰላም ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ ተንታኞቹ ስጋታቸውን ገልጸዋል። እንደ ሱዳን፣ ኤርትራ፣ ሶማሊያ እና ግብፅ ካሉ ጎረቤት አገራት ጋር የሚነሱ ውጥረቶች ሁኔታውን ውስብስብ እንደሚያደርጉት በመጠቆም፣ የባህር በር ጥያቄው በቀጣናው ጂኦፖለቲካ ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ ከፍተኛ መሆኑ ተነስቷል።
በመሆኑም በዓለም አቀፍ ሕግና መድረኮች አሠራር መሠረት የባህር በር ባለቤት የሆኑ አገራትን ሉዓላዊ መብት ማክበር አስፈላጊ መሆኑን የቀድሞው የአውሮፓ ህብረት መልክተኛ ገልጸዋል።
የባህር በር ማግኘት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ዕድገት አስፈላጊ ቢሆንም፣ ሂደቱ የአጎራባች አገራትን ሉዓላዊነት ባከበረ መልኩ በሰላማዊ መንገድ ሊከናወን እንደሚገባ ነው ያነሱት።
በዘዴቪድ ኸርስት ፖድካስት ላይ የቀረቡት አምባሳደር አሌክስአንደር ሮንዶስ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ የሚሆነው ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር ያላትን የዲፕሎማሲ ግንኙነትና የኢኮኖሚ ትስስር ማጠናከር እንደሆነ ተቁመው፤ በሰላማዊ ውይይት ላይ የተመሠረተ የጋራ መግባባት በመፍጠር፣ በቀጣናው ዘላቂ ሰላምና የጋራ እድገትን ማረጋገጥ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ በአለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዘንድ ሰፊ ትኩረትና ተቀባይነትን በማግኘት ላይ ነው ።
በ ታደለ ገበየሁ












