የኢትዮጵያ የቀይ ባህር ጥያቄ ከወደብ አጠቃቀምና ከንግድ እንቅስቃሴ ባለፈ፣ ከሀገሪቱ ታሪካዊ መብቶች፣ ከብሔራዊ ደህንነት፣ ከዕድገት ፍላጎት እና የቀጣናው ጸጥታ ጋር በጥልቀት የተሳሰረ መሆኑ ዓለም አቀፍ ትኩረት እየሳበ መምጣቱ ይታወቃል። ጉዳዩ አሁን ላይ በተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን እና በታዋቂ የፖለቲካ ተንታኞች ዘንድ የትኩረት ማዕከል ሁኗል።
በዚህ ረገድ ታዋቂው ዓለም አቀፍ ሚዲያ “ሚድል ኢስት አይ” ፤ በ “ዘ ዴቪድ ኸርስት ፖድካስት” ላይ በቀረበው ሰፊ ትንታኔ፤ የኢትዮጵያን የባህር በር ፍላጎት፣ ታሪካዊ ዳራዎች፣ ኢኮኖሚያዊ አስፈላጊነት እና ጂኦፖለቲካዊ መስተጋብሮች በሰፊው ተንስቷል።

በዚህ ውይይት ላይ በመካከለኛው ምሥራቅና በአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ፣ በዲፕሎማሲ እና የተለያዩ ሃገራትን በማደራደር የብዙ ዓመታት ልምድ ያላቸው ታዋቂው የጂኦፖለቲካ ተንታኝ እንዲሁም አምባሳደር አሌክሳደር ሮንዶስ ሃሳባቸውን አካፍለዋል። አምባሳደሩ ከኢትዮጵያ የቀይ ባህር ጥያቄ ጎን ለጎን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ የነበሩ ወቅታዊ ሁኔታዎች እና የቀጣናውን ፖለቲካ በሰፊው አብራርተዋል።
በውይይቱ ላይ በሰፊው እንደተነሳው፤ የኢትዮጵያ የቀይ ባህር ፍላጎት መሠረቱ በሀገሪቱ ረጅም ታሪክ፣ በሕዝብ ብዛት እና በማደግ ላይ ባለው ኢኮኖሚያዊ ፍላጎት የተደገፈ ነው። ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት እና በየብስ የተከበበችው ኢትዮጵያ ከኤርትራ መገንጠል በኋላ የባህር በር አልባ መሆኗ በውጭ ንግዷ፣ በወጪና ገቢ ሸቀጦች ማጓጓዝ እንዲሁም አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገቷ ላይ ከፍተኛ ጫና እያደረገ መሆኑ ተመላክቷል። በመሆኑም የባህር በር ጥያቄው ለአሁን ጊዜ ብቻ ሳይሆን፣ ለቀጣይ የሀገሪቱ የልማት፣ የንግድና የደህንነት ዋስትና ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑ ገልፀዋል።
በሌላ በኩል በዓለም አቀፍ ውሃዎች ላይ የመንቀሳቀስና የመጠቀም መብት የሀገራት የጋራ መርህ መሆኑ አንስተው፣ እንደ አሜሪካና ቻይና ያሉ ሃያላን ሀገሮች የባህር መስመሮችን ለንግድና ለተለያዩ ፍጆታዎች እንደሚጠቀሙበት ሁሉ፣ ኢትዮጵያም የመጠቀም መብት እንዳላት አንስተዋል።

የቀይ ባህር ጉዳይ ከአንድ ሀገር ፍላጎት አልፎ የቀጣናውን የደህንነት ሚዛን የሚነካ በመሆኑ፤ ከግብጽ፣ ከኤርትራ እና ከሶማሊያ ጋር የሚደረጉ ግንኙነቶች እና የጥምረት ሂደቶች በአፍሪካ ቀንድ ያለውን ሰላም እንደሚቀርጹት ነው የጠቀሱት።
የኢትዮጵያ የቀይ ባህር ፍላጎት በሕግ፣ በድርድርና በጋራ ጥቅም መርሆዎች ላይ ተመስርቶ መታየቱ ለአካባቢው ሰላም እና መረጋጋት ትልቅ ሚና እንደሚኖረውም ተገልጿል።












