በአሜሪካ የሚካሄደው የአጋማሽ ዘመን ምርጫ የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን አስተዳደር የፖለቲካ አቅምና የወደፊት ውሳኔዎች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንዳለው ተገለጸ። የምርጫው ውጤት በአሜሪካ ውስጣዊ ፖለቲካ ብቻ ሳይወሰን፣ በዩክሬን ጦርነት፣ በኢራን ጉዳይና በዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ላይም ትልቅ አንድምታ እንደሚኖረው ተብራርቷል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር የሆኑት ትዕዛዙ መሐመድ በNBC ኢትዮጵያ የ“ዓለም አቀፍ” ፕሮግራም ላይ በመቅረብ ስለምርጫው ሰፋ ያለ ማብራሪያቸውን ሰጥተዋል።
መምህሩ እንዳብራሩት፣ የአጋማሽ ዘመን ምርጫው በኮንግረሱ ውስጥ አብላጫ ድምፅ የሚያገኘውን ፓርቲ በመወሰን፣ ሕጎችን በማፅደቅ፣ በጀትን በመወሰንና የመንግሥትን ሥራ በመቆጣጠር ረገድ ወሳኝ ሚና አለው። በመሆኑም ምርጫው በፕሬዝዳንቱ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት አፈጻጸም ላይ የሚሰጡት የፖለቲካ ዳኝነት እንደሆነ ተናግረዋል።

ስለአሜሪካ የምርጫ ሥርዓት ሲያብራሩም፣ ፕሬዝዳንቱ በየአራት ዓመቱ እንደሚመረጥ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ደግሞ በየሁለት ዓመቱ እንደሚመረጡ አስረድተዋል። በተጨማሪም በሴኔትም ከሚገኙት አባላት አንድ ሦስተኛው በየሁለት ዓመቱ ይመረጣሉ ነው ያሉት።
የሀገሪቱ የመንግሥት አወቃቀር ሦስቱ የሥልጣን አካላት (ሕግ አውጪ፣ ሕግ አስፈጻሚና ሕግ ተርጓሚ) እርስ በርስ በመቆጣጠርና የሥልጣን ሚዛንን በመጠበቅ እንደሚሠሩ ያብራሩት መምህሩ፣ ዲሞክራቶች በኮንግረሱ አብላጫ ድምፅ ካገኙ የትራምፕ አስተዳደር ውሳኔዎች ለበለጠ ቁጥጥርና ጥያቄ ሊጋለጡ እንደሚችሉ ገልጸዋል። በተለይም በኢሚግሬሽን፣ በአስተዳደሩና በመከላከያ ፖሊሲዎች ላይ ክትትልና ምርመራ ሊጠናከር እንደሚችል አመልክተዋል።
ከውስጣዊ ፖለቲካ ባሻገር፣ የምርጫው ውጤት በውጭ ፖሊሲ ላይም ተፅዕኖ እንደሚኖረው መምህሩ አንስተዋል። በተለይ ለዩክሬን የሚሰጠው የገንዘብና የወታደራዊ ድጋፍ፣ ከሩሲያ ጋር ያለው ግንኙነትና የኢራን ጉዳይ የፓርቲዎቹ የፖለቲካ ልዩነት ሊንጸባረቅባቸው እንደሚችሉ ጠቁመው፣ ኮንግረሱ የመከላከያና የውጭ ድጋፍ በጀቶችን በማፅደቅ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ገልፀዋል።

አያይዘውም ዲሞክራቶቹ ኮንግረሱን
ከተቆጣጠሩ ለዩክሬን የሚሰጠው እና ተቀዛቅዞ የነበረውን ወታደራዊ በጀት እንዲሁም ድጋፍ የማጽደቅ ዕድላቸው ከፍተኛ እንደሚሆን ተናግረዋል።
በተጨማሪም የነዳጅና የሸቀጦች ዋጋ መጨመር እንዲሁም የኑሮ ውድነት በመራጮች ውሳኔ ላይ ተፅዕኖ ከሚያሳድሩ ጉዳዮች መካከል እንደሆኑ መምህሩ ጠቁመዋል። መራጮች ፖለቲከኞች የገቡትን ቃል ኪዳን ብቻ ሳይሆን፣ በዕለት ተዕለት ኑሯቸው ላይ የሚያዩትን ለውጥም እንደሚመዝኑ አብራርተዋል።

የአጋማሽ ዘመን ምርጫው የአሜሪካ ሕዝብ በመንግሥት አፈጻጸም ላይ አቋሙን የሚገልጽበትና የፖለቲካ ሥልጣንን ሚዛን የሚያስጠብቅበት ወሳኝ የዲሞክራሲ ሂደት መሆኑ ተጠቁሟል።
በ-በረከት አስረስ












