
በአባይ ወንዝ መነሻ ኢትዮጵያ እና በወንዙ በታችኛው ተፋሰስ ግብፅ መካከል ያለው ግንኙነት መቼም ቢሆን የጠራ እና ሰላማዊ ሆኖ አያውቅም። የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ከብዙ ሺህ ዓመታት ጀምሮ በሃይማኖታዊ፣ በባህላዊ፣ በጂኦ እና ውሃ ፖለቲካ ሴራዎች የተጠላለፈ ነው።
ባለጸጋዋ እና ስልጡኗ ኢትዮጵያ ታሪካዊ ስልጣኔዋ መዳከሙ፣ ጦርነትን ጨምሮ የዛሬዎቹ ውስብስብ ቀውሶች በአጋጣሚ የመጡ ሳይሆኑ ከዘመናት በፊት ከግብጽ ሴራዎች ጋር የተያያዙ በመሆናቸው ከመካከለኛው ዘመን ጀምሮ ስትታመስ ኖራለች።
ኢትዮጵያ በርካታ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች እና ሰፊ የከርሰ-ምድር ውሃ ሀብት ባለቤት መሆኗ የተፈጥሮ ባለጸጋ እንዳደረጋት ሁሉ፥ በሌላ በኩል በውሃ ፖለቲካ ምክንያት ብዙ ጠላቶችን አፍርታ የውጭ ጣልቃ ገብነቶች ሰለባ እንድትሆን አድርጓታል። ከጥንት ፈርኦኖች እስከ አሁኖቹ መሪዎች ድረስ የግብፅ ዋና ስትራቴጂካዊ ግብ “የአባይን ወንዝ ምንጭ በብቸኝነት መቆጣጠር” ነው።
ይህንን ግብ ለማሳካትም ግብፅ በተለያዩ ዘመናት ከነበሩ ኃይሎች ጋር አብራ ሰርታለች፤ ከመካከለኛው ዘመን ጀምሮ ከማምሉኮች፣ ከኦቶማን ቱርክ እና ከእንግሊዝ ቅኝ ገዢዎች ጋር በመተባበር የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ለመሸርሸር መና የቀረ ጥረት አድርጋለች።
በ17ኛው ክፍለ ዘመን ግብጾች በእስልምና ሃይማኖት ሽፋን በደቡብ አቅጣጫ ወደ ሱዳን በመግባት የአባይን ሸለቆ ለመቆጣጠር ያደረጉት ሙከራ የከሸፈ ሲሆን፥ የኦቶማን ቱርክን ቀጥተኛ ድጋፍ በማገኘት በቀይ ባህር በኩል ያደረጓቸው ወረራዎችም አልተሳኩም።
ከግብፅ ጋር የነበረው የ1600 ዓመታት የጳጳሳት ግንኙነት የሀገሪቱን የሊቃውንትና የምሁራን እድገት የገደበ ብሎም ከዓለም ጋር ያላትን የንግድና የቴክኖሎጂ ትስስር በማዳከም ለድህነት የራሱን አሉታዊ አስተዋጽኦ ያበረከተ ቢሆንም፥ በወቅቱ የነበረውን የሀገሪቱን ህልውና በማስቀጠል ረገድ የነበረው ሚና ቀላል አልነበረም። ይህም ያበቃው በ1950ዎቹ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የመጀመሪያውን ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ በሾመችበት ወቅት ነበር።
በ1960 እ.ኤ.አ. የኤርትራ የነጻነት ግንባር ሲመሰረት፥ ግብጾች ኢትዮጵያን ለመከፋፈል በነበራቸው አላማ ዋና ጽሕፈት ቤታቸው ካይሮ ላይ እንዲሆን በማድረግ ለቡድኑ ድጋፍ ከማድረጋቸውም በላይ ”የአረብ ድምፅ” የተሰኘውን የካይሮ ሬዲዮ ጣቢያ በመስጠት በኢትዮጵያ ላይ የስነ-ልቦና ጦርነት እና የመከፋፈልን ፕሮፓጋንዳ እንዲነዛ አድርገዋል። በተመሳሳይ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) እና የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) በትግል ላይ በነበሩበት ወቅት መሪዎቻቸው ካይሮ ውስጥ ዲፕሎማሲያዊ ቢሮ እንዲከፍቱ ተደርጓል።
በቅርቡም በሰሜን ኢትዮጵያ በተከሰቱት ግጭቶች ግብፆች ለህወሓት ከፍተኛ ድጋፍ በማድረግ የግጭቱ ጠንሳሽ እና መሪ በመሆን የአባይን ራስ በመቆጣጠር በሀገሪቱ የተረጋጋ ምህዳር እና ኢኮኖሚያዊ አቅም የማሳጣት የሺህ ዘመን ህልማቸውን ለማሳካት የሄዱበት ርቀት በሽንፈት ተጠናቋል።
ዛሬ ላይ የኢትዮጵያን ብሩህ ህልም እውን ለማድረግ የአባይን እንቆቅልሽ በታላቁ ህዳሴ ግድብ እና በልማት መፍታት ብቻ ሳይሆን፥ ከታሪክ በመማር ከውጭ የሚመጡ የፖለቲካ ሴራዎችን በህዝብ አንድነትና በንቃት መመከት ወሳኝ ነው።
በ- የአብሥራ ተፈራ












