
የቀድሞው በኬኒያ የኢትዮጵያ አምባሳደር እና የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ጀነራል ባጫ ደበሌ ከስድስት ዓመታት በፊት በሰሜን እዝ ላይ የተፈጸመውን ታሪካዊ ክህደት እና ህወሃት የደረሰበትን ከፍተኛ ውድቀት በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ጥቅምት 24 ከተፈጸመውን አሰቃቂ ድርጊት በፊት የነበረውን ሁነት ጀነራሉ ሲያስታውሱ፤ ጦርነቱ ከመቀስቀሱ በፊት የመከላከያ ሠራዊቱን በአዲስ መዋቅር ለማደራጀት እና ከሰሜን እዝ የሰው ኃይልና መሳሪያዎች ወደ መሃል ሀገር ለማስወጣት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ የሕወሓት አመራሮች ሕፃናትንና አረጋውያንን ከፊት በማሰለፍ ሰራዊቱና መሣሪያዎቹ እንዳይወጡ በኃይል ከልክለዋል።
ይሄን ተከትሎም በየክፍለ ጦሩ «የተሃድሶ ግብዣ» በሚል ሽፋን የሠራዊቱን አባላት በማዘናጋት እና ጥቃት በመፈጸም በይፋ ጦርነት መጀመራቸውን ገልጸዋል። በመቀጠልም ከፌዴራል መንግስት የተላከውን 1.5 ቢሊዮን ብር ከመቀሌ ኤርፖርት በመዝረፍ እንዲሁም አዛዦችን በማሰር ህገወጥ ድርጊታቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውንም አስታውሰዋል፡፡

የተፈጸመው ህገ ወጥ ድርጊት «በዓለም ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የጭካኔ ጥግ» መሆኑን ያመላከቱት ጀነራሉ፣ የሠራዊቱ አባላት በተኙበት መታረዳቸውን፣ አስከሬናቸው ለአሞራና ለጅብ መጣሉን፣ ሴት የሠራዊቱ አባላት በአሰቃቂ ሁኔታ መደፈራቸውን ጨምሮ በርካታ ኢ-ሰብአዊ የሆኑ ድርጊቶችን መፈጸማቸውን ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ የመከላከያ ሰራዊቱ በፍጥነት ራሱን በማደራጀት የመከላከል እና መልሶ የማጥቃት እንቅስቃሴውን በማጠናከር በሶስት ሳምንታት ውስጥ የመቀሌን ከተማ መቆጣጠር መቻሉን ጀነራሉ ያስታወሳሉ፡፡
ህወሓት ከጅምሩ ለውጪ ኃይሎች የተገዛ «ቅጥረኛ ድርጅት» መሆኑን ገልፀው፣ አሁን ላይ የትግራይ ሕዝብ የቡድኑን አጥፊነት ተረድቶ ከመንግስት ጐን በመቆም እያጋለጣቸው መሆኑን ነው የጠቆሙት።
ጀነራሉ በመልዕክታቸው፤ በየመዋቅሩ ያለው የሕወሓት የፖለቲካ አስተሳሰብ ሙሉ በሙሉ መጸዳት እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተው፣ የትግራይ ወጣት ከጥፋት አዙሪት በመውጣት ከተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ወደ ሰላምና ልማት መመለስ እንዳለበት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ጀነራል ባጫ ደበሌ ጥቅምት 24ን ለመዘከር በኤንቢሲ ኢትዮጵያ “ጊዜ ግስ” ፕሮግራም ላይ በነበራቸው ቆይታ፣ በወቅቱ የተፈጠሩትን ለጆሮ የሚከብዱ ድርጊቶች እና የመከላከያ ሰራዊቱን ብስለት የተሞላበት መከላከል እንዲሁም የፌዴራል መንግስት የከፋ ጥፋት እንዳይደርስ ያደረገበት መንገድ አስመልክተው በስፋት አጋርተዋል፡፡
በ – የአብሥራ ተፈራ












