በኔፓል ኤቨረስት ተራራ አቅራቢያ በሚገኝ በበረዶ በተሸፈነ የሄሊኮፕተር ማረፊያ ላይ ለማረፍ ሲሞክሩ የነበሩ ሁለት ሄሊኮፕተሮች በአየር ላይ በመጋጨታቸው ቢያንስ የአንድ ሰው ሕይወት ሲያልፍ፣ በሦስት ሰዎች ላይ ደግሞ ጉዳት ደርሷል።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የሄሊኮፕተሮቹ ማሽከርከሪያ ክንፎች እርስ በእርስ ሲመታቱና ሁለቱም አውሮፕላኖች መሬት ላይ መከስከሳሳቸው ተገልጿል። ይህም በአቅራቢያው የነበሩ ቱሪስቶች ለደህንነታቸው ሲሉ አከባቢውን ጥለው ለመሸሽ ተገደዋል።
ግጭቱ የተከሰተው በኔፓል ሶሉክሁምቡ ክልል በሚገኘው ፌሪቼ በተባለ ስፍራ በሀገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር ከጠዋቱ 8:11 ገደማ ሲሆን፤ አደጋው የደረሰው በ”ፊሽቴል ኤር” እና በ”ኤር ዳይናስቲ” በሚንቀሳቀሱ ሄሊኮፕተሮች መካከል ነው።
የአካባቢው ፖሊስ እንደገለጸው፣ ሕይወቱ ያለፈው ግለሰብ የ47 ዓመት ህንዳዊ ቱሪስት ሲሆኑ፣ በተጨማሪም የ49 ዓመት ኒውዚላንዳዊ ተጓዥ እና ሁለት ኔፓላዉያን አብራሪዎች ተጎድተዋል።

የተጎዱት ሰዎች ወደሕክምና ተቋማት የተወሰዱት ሲሆን፣ የኔፓል ሲቪል ኤቪዬሽን ባለስልጣንም ከአደጋው ሁኔታ ጋር ተያይዞ ምርመራ ጀምሯል።
አደጋው የተከሰተበት ፌሪቼ ወደ ኤቨረስት ተራራ ቤዝ ካምፕ በሚወስደው የእግር መንገድ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በዚህ ስፍራ ሄሊኮፕተሮች ቱሪስቶችን፣ ተራራ ወጪዎችንና ቁሳቁሶችን ለማጓጓዝ እንዲሁም አስቸኳይ የህክምና እገዛዎችን ለማድረግ በቋሚነት ያገለግላሉ።












