NBC ETHIOPIA
በረከት አስረስ
በዓለም አቀፍ ፖለቲካ የኃይል ሚዛን እየተቀየረ ባለበት በዚህ ወቅት፣ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚከሰቱ ግጭቶችና የሀገራት የሚያሳዩት የጥቅም ፉክክር አዳዲስ የዲፕሎማሲ ፈተናዎችን እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል። በተለይም የቀይ ባህር ጂኦፖለቲካ፣ የዓባይ ውሃ ደህንነትና የኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎት በቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ የወቅቱ ርዕሰ ጉዳዮች ሆነዋል።
በ NBC Ethiopia “ዓለም አቀፍ” ፕሮግራም ላይ ተባባሪ አቅራቢ የሆኑት እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ትዕዛዙ መሐመድ እነዚህንና ሌሎች ወቅታዊ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያ ሀሳባቸውን አካፍለዋል።

በሶስተኛው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ የላቀ ዲፕሎማሲያዊ ሞገስና ተቀባይነት ማግኘቷ ተመላክቷል። መምህሩ እንዳመለከቱት፣ ሀገሪቱ ከሩሲያ እንደ SU-35 የጦር አውሮፕላን እና S-400 የአየር መከላከያ ሥርዓት ያላቸውን ዘመናዊ መሣሪያዎችን ከሌሎች ሃገር ቀድማ ማግኘቷ የሁለቱን ሃገራት ግንኙነት መጠንከሩን ያመለክታል ብለዋል።

በተጨማሪ በቀይ ባህር ዙሪያ የሚታዩ ጂኦ-ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ከፍተኛ ውዝግብ እየፈጠሩ እንደሆነ ተነስቷል። እንደ ፖለቲካ ምሁሩ ገለጻ፣ የግብፁ ፕሬዝዳንት «ቀይ ባህር ወታደራዊ መሆን የለበትም» ማለታቸው ፍጹም ግብዝነት ነው። አሜሪካ እና ሌሎች ሀገራት በቀይ ባህር ዙሪያ በርካታ ወታደራዊ ካምፖች ሲኖሯቸው ግብፅ ድምጿን አጥፍታ፣ ኢትዮጵያ የባህር በር ተጠቃሚነትን ስትጠይቅ ግን ያልተገባ አስተያየት መስጠታቸው የኢትዮጵያን የባህር በር ፍላጎት ለማፈን የተለመደ ሴራ መሆኑን አጋልጠዋል።
በዓባይ ወንዝ አጠቃቀም ዙሪያም ከባድ አለመግባባቶች መኖራቸውን መምህሩ ጠቁመው፣ ግብፅ 86 በመቶ የውሃ አስተዋጽኦ የምታበረክተውን ኢትዮጵያ “አንድ ጠብታ ውሃ መጠቀም አትችልም” ማለቷ ታይቶ የማይታወቅ ስግብግብነት መሆኑን ተችተዋል።

በመካከለኛው ምስራቅ የእስራኤል ምርጫና የፖለቲካ ጥምረቶች ለቀጠናው የሰላምና ደህንነት ሁኔታ ያላቸውን ተፅዕኖ መምህር ትዕዛዙ፣ በተመሳሳይ በአሜሪካ የሚካሄዱ የመካከለኛ ዘመን ምርጫዎች የፕሬዚዳንቱን የፖለቲካ ተፅዕኖና በኮንግረሱ ያለውን የኃይል ሚዛን ሊቀይሩ እንደሚችሉ ገልጸዋል። ይህም በኢራንና በመካከለኛው ምስራቅ ላይ የአሜሪካ ፖሊሲ አቅጣጫን ሊወስን የሚችል ጉዳይ መሆኑን አብራርተዋል።
በሌላ በኩል የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ከሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ባለፈ በአውሮፓ ደህንነት፣ በኃይል አቅርቦትና በዓለም ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው ያሉት የፖለቲካ ምሁሩ፣ ጦርነቱ በሩሲያና በምዕራባውያን መካከል ያለውን ውጥረት ከማሳየቱም በላይ በዓለም አቀፍ የኃይል ሚዛን ላይ ለውጥ እያመጣ ይገኛል። በኤዥያ ፓሲፊክ በኩልም ጃፓን የመከላከያ አቅሟን ለማጠናከር እየሰራች ሲሆን፣ የሰሜን ኮሪያ ሚሳኤል ሙከራዎች በክልሉ ያለውን ውጥረት እያባባሱት እንደሆነ ጠቁመዋል።

በማጠቃለያቸውም፣ ኢትዮጵያ በቀጣናው ከሚሰነዘሩባት የጂኦ-ፖለቲካ ማዕበሎች እና የከበባ ሙከራዎች ለመውጣት ሁለንተናዊ ዝግጅት ማድረግ እንዳለባት አንስተው፤ በሀገር ውስጥ የፖለቲካ ልዩነቶች ቢኖሩም፤ የሀገር ሉዓላዊነትን እና የተፈጥሮ ሀብትን የማልማት መብትን አስመልክቶ ኢትዮጵያውያን ሁሉንም ልዩነቶች በመተው በአንድነት መቆም እንደሚገባቸው አንስተዋል።












