
በአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ ውስጥ የቀይ ባህር ጉዳይ እና የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የህልውና አጀንዳ ሆኖ ቀጥሏል። በNBC አለም-አቀፍ ፕሮግራም ላይ የተደረገው ውይይት፣ የኢትዮጵያን የወደብ ጥያቄ ፍትሃዊነት እና የቀጠናውን ውስብስብ ሴራ በአዲስ መነጽር ፈትሾታል።
በውይይቱ ላይ የጂኦፖለቲካ ተንታኙና የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎች ጸሃፊው አቶ ተስፋዬ ፋንታሁን እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ አቶ ትዕዛዙ መሐመድ በስፋት አብራርተዋል።
አቶ ተስፋዬ፣ የአሁኗን የአሰብ ወደብ ገጽታ “ሳይተኮስባት የፈረሰች ከተማ” ሲሉ ይገልጿታል። አሰብ በአሁኑ ወቅት ምንም ዓይነት የጎላ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሌለባት ቦታ መሆኗንም ጨምረው ገልፀዋል።

“በማንኛውም ሀገር የመሬት መቀማትና መሰጠት በውጭ ተጽዕኖ ሊከሰት ይችላል፣ የእኛን ሃገር ጉዳይ ግን ለየት የሚያደርገው የራሳችን መሪዎች ‘ባህር አንፈልግም’ ብለው የሰጡበት መንገድ ነው” ያሉት ደግሞ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ ትዕዛዙ፣ ሃሳባቸውን ሲያጠናክሩ፣ ኢህአዴግ ስልጣን በያዘበት ወቅት ለኤርትራ ጥቅም ያደላ ፖሊሲ ይከተል እንደነበርና ይህም አገሪቱን የጂኦግራፊ እስረኛ እንዳደረጋት ያብራራሉ።
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ፍትሃዊነትን ስያስረዱም ታላላቅ አገራትን በምሳሌነት ያነሳሉ። አሜሪካ ለብሔራዊ ጥቅሟ ስትል በብዙ ሺህ ማይሎች ርቃ በመሄድ በሆርሙዝ ሰርጥ በምታደርገው ውጊያ ላይ እጇን በምታስገባበት ዓለም፣ ከባህር ዳርቻው በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኘውና ሰፊ ህዝብ ያላት ኢትዮጵያ “ተዘግተሽ ተቀመጪ” መባሏ በፍጹም ውሃ የሚነሳ ሃሳብ አይደለም ይላሉ።

በቀይ ባህር እና በአፍሪካ ቀንድ የሚከሰቱ ችግሮች ሁሉ ኢትዮጵያን በቀጥታ እንደሚነካት ያነሱት ምሁሩ “ጉዳቱ እና ችግሩ የማያጣን ከሆነ ከጥቅሙም ተቋዳሽ መሆን አለብን” የሚለው መርህ የኢትዮጵያ የስትራቴጂክ ጥያቄ መሆን እንዳለበት ይጠቅሳሉ።
ጤናማ ያልሆነዉን የግብፅን ወቅታዊ የጂኦፖለቲካ አካሄድ አስመልክቶ አቶ ተስፋዬ ሲናገሩ፤ ኢትዮጵያ የባህር በር ካገኘች የኢኮኖሚ አቅሟ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያድግ የምታውቀው ካይሮ ይህ እንዳይሆን በዲፕሎማሲውና በቀጠናው ፖለቲካ ላይ እንቅፋት መሆኗን ቀጥላለች። ግብፅ የምታራምደው ስውር ስሌት “ኢትዮጵያ የባህር በር ካጣች በድህነት ትቀጥላለች፤ ድሃ ከሆነች ደግሞ ታላቁን የአባይ ግድብ በአግባቡ ገንብታ ማጠናቀቅና ማስተዳደር አትችልም” የሚል መሆኑን ይናገራሉ።
ምሁራኑ እንደሚስማሙት፣ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የጦርነት አዋጅ ሳይሆን በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሰረተ ፍጹም ሰላማዊ ጥያቄ ነው። አገራት በታሪካቸው የመሬት ልውውጥና የወደብ ድርድር ማድረጋቸው ዓለም አቀፍ ህግ የሚደግፈውና የተለመደ አሰራር መሆኑን ያነሳሉ።
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ድምጿ ተሰሚ እንዲሆን መከተል ያለባትን የቤት ስራዎችን በተመለከተ አቶ ተስፋዬ፣ ሲያስቀምጡ የሀገር ውስጥ ፖለቲካን ማረጋጋት፣ ኢኮኖሚን ማሳደግ እና የመከላከያ ተቋማትን ማጠናከር ቀዳሚ ተግባራት ናቸው ይላሉ።አማራጭ ወደቦችን በብልሃትና በድርድር መጠቀም የሚያስችሉ የዲፕሎማሲ መንገዶችን በጽናት መከተልም ዋነኛው መፍትሄ መሆኑን አጽኖት ሰጥተው ጠቅሰዋል፡፡
በ – በረከት አስረስ












