NBCETHIOPIA
በ – በረከት አስረስ
የቀይ ባሕርና የአፍሪካ ቀንድ ቀጠና እንደወትሮው ሁሉ ዛሬም በፖለቲካ ትኩሳት እና በወታደራዊ ውጥረቶች እየተናወጡ ይገኛሉ። አሁናዊ የፖለቲካ መለዋወጥ የቀጠናውን መልክ በፍጥነት እየቀየረው ይገኛል፡፡ በወቅታዊ፣ ዓለም አቀፋና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት የሚያደረግው ኤንቢሲ ዓለም-አቀፍ የአካባቢውን ሁኔታ በተመለከተ በጥልቀት ዳሧል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፋዊ ግንኙነት መምህር የሆኑት ትዕዛዙ ሙሀመድ የቀጠናውን ሁኔታ ሲያሥረዱ፣ በተለይ ከሰሞኑ የሚታየው የሰሜን ኢትዮጵያ አለመረጋጋት መስመር መያዙ ለኢትዮጵያ የልማትና የብልጽግና ጉዞ ትልቅ ዕፎይታን የፈጠረ የቅርብ ጊዜ ክስተት ነው። ይህም በሰሜኑ ጦርነት የታየው አዲስ ተሞክሮ የሀገሪቱን የደህንነት ተቋማት የመፈጸም አቅም ማደግን በግልጽ ያሳየበት ነበር ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ የውስጥ ችግሮች መልክ መያዝ ሀገሪቱ ከሌሎች ሃገራት ጋር ለምታደርገው የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ያላትን ዓለም አቀፍ ተሰሚነት ያጠናከረችበት እንደሆነ የጠቀሱት መምህሩ፣ በጎረቤት ሀገራት ዘንድ ግን ያለው አለመረጋጋቱ አሁንም መቀጠሉ ለቀጠናው ስጋት ነው ብለዋል፡፡

እንደ ማሳያም የሻዕቢያ አስተዳደር ከዓለም የራቀበትን ደካማ ዲፕሎማሲ የጠቀሱት የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ፣ ኤርትራ ከዩናይትድ ኪንግደም ጋር በገባችበት እሰጣ ገባ ምክንያት የተጣለበት ማዕቀብ የሀገሪቱን ገጽታ በይበልጥ እያበላሸው ይገኛል ነው ያሉት። በሌላ በኩል ሱዳን በግብፅ ድንበር አካባቢ ንፁሃንን ሰለባ ባደረጉ የድሮን ጥቃቶች እና በርስ በእርስ ጦርነት መታመሷ ሌላው የቀጠናው አለመረጋጋት ማሳያ ነው ሲሉ ያብራሩት፡፡
አያይዘውም ሱዳን የራሷን የውስጥ ችግሮችን ሳታስተካክል በኢትዮጵያ ላይ በሚደረጉ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች ላይ አብራ መሰለፏ አግራሞትን የሚያጭር ጉዳይሲሆን፣ በተመሳሳይ ሞቃዲሾም ከአልሸባብ ጋር ያለባትን የጸጥታ ቀውስና የእርስ በእርስ ጦርነትን ፈር ማስያዝ ተስኗታል ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢትዮጵያ በአባይ ውሃ አጠቃቀምና የባሕር በር ማግኘት ላይ ያላት ፖሊሲ በዓለም-አቀፍ ደረጃ ሰፊ ድጋፍ እያገኘ መምጣቱ የታየበት ነበር። ሀገሪቱ የምትከተለው ሰጥቶ የመቀበል መርህ የአውሮፓና የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራትን ድጋፍን እያስገኘላት ነው፡፡
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ የባሕር ኃይል ምስረታ ከፈረንሳይ መንግሥት ትልቅ ድጋፍ እያገኘ መሆኑ እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የአሜሪካው የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርክ ሩቢዮ በስልክ መወያየታቸውም ለኢትዮጵያ የተፈጠረውን በጎ ዓለም-አቀፍ አውድ ያሳያል።
በቀጠናው ፖለቲካ ላይ ሌላው ትልቅ አቅም የፈጠረው የሶማሌላንድ ወቅታዊና ፅኑ አቋም ነው። የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት አብዱራህማን መሐመድ አብዱላሂ ወደ አረብ ኤምሬቶችና አሜሪካ ካደረጉት ጉዞ መልስ፣ በቅርቡ በኤል አላሚን የተደረገው የአራቱ ሀገራት አቋም ተገቢ ያልሆነና ኢትዮጵያን የሚጎዳ ነው በማለት በይፋ ተቃውመዋል። አያይዘውም ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ያላትን አጋርነት አጽኖት ሰጥተውበታል፡፡
በአጠቃላይ በኤንቢሲ ዓለም-አቀፍ በርካታ አህጉራዊና ዓለም-አቀፋዊ ጉዳዮችን የተዳሰሱበት እና የቀጠናውን መጻኢ እድል የተጠቆመበት ውይይት ነበር፡፡













