በኤንቢሲ ኢትዮጵያ «ጊዜ ግስ» ፕሮግራም ላይ ቆይታ ያደረጉት የቀድሞ የትግራይ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር እና የመከላከያ አባል ሜጀር ጀነራል ገብረ አድሃና (ገብረ ዲላ)፣ ህውሃት በትግራይ ህዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል እንደፈጸመ እና መጠየቅ እንዳለበትም ተናግረዋል::
“ውጊያውን የሚመሩት አካላት ለማይወጡት ነገር እርግጠኞች ሳይሆኑ ይህንን ሁሉ መስዋዕት ከመክፈላቸው በፊት አንዋጋም ማለት ነበረባቸው” ያሉት ጀነራል ውጤቱን ቀድመው እንደሚያውቁት አስረድተዋል::
የህወሃት ሳያንስ ሌሎች የጥፋት ሃይሎችን በመጋበዝ ህዝቡ ላይ አስከፊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶች አድርሷል:: ይህም የነበረውን ድጋፍ እንዲያጣና ተበታትኖ እንዲቀር አድርጎታል:: ወጣቱ በግዳጅ መሰለፉን ያነሱት ጀነራሉ ይህን የሽብር ሃይል ከስንቅ ጀምሮ የቤተሰቡን ህይወት እየገበረ ሲደግፈው የነበረው ማህበረሰብ፣ አሁን ላይ የቻለ በመሸሽ ያልቻለ ደግሞ እጅ እየሰጠ ብቻውን አስቀርቶታል::
በርካታ ወጣቶች ይህንን አላስፈላጊ ጦርነት በመሸሽ ከቀያቸው መሰደዳቸውን ያነሱት ጀነራሉ፣ ሁኔታውን ሲያስረዱ “መቀሌ ላይ ወጣት የለም” ሲሉ በሃዘን እና በምሬት ይገልጻሉ::
በህወሃት የሚጠነሰሱት የሽብርተኝነት እቅዶች፣ ራሱን “ፅምዶ” ብሎ በሚጠራው ቡድን አስፈጻሚነት በማህበረሰቡ ላይ አልፎም በሃገሪቱ ላይ ሲያደርስ ከነበረው በደል በተጨማሪ ከባዕዳን ጋር በመቀናጀት ኢትዮጵያን ለማፍረስ እንደሚሰሩ አስታውሰዋል::
በሌላ በኩል የ“ፅምዶ”ን ዓላማ የማይቀበሉት ሜጀር ጀነራል ገብረ አድሃና፣ ይህም ከህወሃት እንዲለቁ ምክንያት ሆኗቸዋል፡፡ ለትግራይ ህዝብ መሞት፣ መሰደድ እና ለደረሰበት በደል ተጠያቂ የማደርገው ህወሃትን ነው ሲሉ አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል::
አክለውም በክልሉ ለጥፋት ዓላማ ሊውሉ የተከማቹት መሳሪያዎች ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት እና ከተላላኪዎቻቸው ሲሆን፣ አብዛኛዎቹ መሳሪያዎችም አገልግሎት ላይ ሳይውሉ መማረካቸውን አስታውሰዋል::
በ-የአብሥራ ተፈራ













