
የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ አመሰራረትና አመጣጥ በድንገት የተከሰተ ሳይሆን፣ የዓለም ሳይንቲስቶች ባደረጉት ረጅም ሂደትና ደረጃ በደረጃ የተገነቡ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን አልፎ የተፈጠረ ነው።
ለመጀመሪያ ጊዜ በበርሊን ጀርመን እንደተካሄደ የሚነገረው የcop1 ጉባኤ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ንቁ ተሳትፎ ዛሬም ድርስ እየተከናወነ ይገኛል ።ምንም እንኳን የሁሉም የCOP ጉባኤዎች አጠቃላይ ግብ የአየር ንብረት ለውጥን መከላከል ቢሆንም፣ በየዓመቱ የውይይት መድረኩ በተለያዩ ሀገራት ይካሄዳል።
በቱርክዬ የተካሄደው COP31 በታዳሽ ኃይል መስፋፋት፣ ለአየር ንብረት ለውጥ መርሀግብር የፋይናንስ አቅርቦት እና በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት የቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ትኩረት እየተደረገ ይገኛል። በጉባኤውም ከነዳጅ ወደ ታዳሽ ኃይል አጠቃቀም የሚደረገውን ሽግግር በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ፤ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችሉ ከተሞችን መገንባት፤ ከበካይ ጋዝ ልቀት ቅነሳ ግቦች ጎን ለጎን ለአጭር ጊዜ ከፍተኛ የሙቀት መጨመር ሂደትን የሚያስከትሉ እንደ ሚቴን ያሉ በካይ ጋዞችን መቆጣጠር እና የቆሻሻ መጠንን መቀነስ የሚሉ ጉዳዮች ተካተውበታል።

በዚህ ስብሰባ ላይ ታዳጊ ሀገራት የሙቀት አማቂ ጋዞችን በመቀነስ ሂደት የሚያጋጥማቸውን የፋይናንስ እጥረት ለመቅረፍ የሚያስችሉ አዳዲስ የገንዘብ ድጋፍ ስምምነቶች የተደረጉ ሲሆን፣ ቱርክዬም የራሷን የንጹህ ኃይል አጠቃቀም ተሞክሮ ለዓለም በማካፈል የዓለም አቀፍ ትብብር አስፈላጊነትን አስምራበታለች።
ጉባኤው የዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥን ለመግታት የታቀዱ ግቦችን ከወረቀት ወደ ተግባር ለማሸጋገር ትልቅ መሰረት የጣለ ነው ተብሏል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ጌዲዮን ጢሞትዮስ በቱርኪዬ አንታሊያ እየተካሄደ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የ31ኛው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP31) ላይ የኢትዮጵያን ልዑክ በከፍተኛ ደረጃ እየመሩ ይገኛሉ። ኢትዮጵያ ቀጣዩን የ32ኛውን የ COP ጉባኤ (COP32) በአዲስ አበባ ለማስተናገድ የምታደርገውን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችና የሽግግር ሂደት እንዲሁም ተመራጭ መሆኗን በይፋ አስተዋውቀዋል።
ኢትዮጵያ ቀጣዩን የCOP32 ለማዘጋጀት መመረጧ በአፍሪካ አህጉር ብቻ ሳይሆን በአለም አቀፍ ደረጃ የሚጠበቅ አጋጣሚ ሆኗል። አዲስ አበባ የዲፕሎማሲ ማዕከል በመሆኗና አገሪቱም በዘላቂ ልማት ዙሪያ ባላት ቁርጠኝነት የተነሳ፣ ይህንን ግዙፍ አለም አቀፍ ጉባኤ ማስተናገዷ ቀጠናዊ እና አህጉራዊ ተሳትፎዋን ይበልጥ ያጎላዋል።
ኢትዮጵያ ጉባኤውን ለማዘጋጀት የምታደርገው ቅድመ ዝግጅት የዲፕሎማቲክ ተጽዕኖዋን ከመጨመር ባሻገር፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገሩ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂዎቿን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማስተዋወቅ ትልቅ እድል ይፈጥርላታል።
ከዲፕሎማሲያዊ እና ፖለቲካዊ ዝግጅቶች ጎን ለጎን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ዓለም አቀፍ ተወካዮችን፣ የሀገር መሪዎችን እና የአየር ንብረት ባለሙያዎችን ለማስተናገድ የሚያስችል አስተማማኝ የአደረጃጀት እና የደህንነት ስርዓት በመዘርጋት ላይ ትኩረት ተደርጓል።
ይህ ዝግጅት የኢትዮጵያን የኮንፈረንስ ቱሪዝም (MICE) አቅም ወደ ከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሸጋግረው ይጠበቃል።በCOP32 ዝግጅት ወቅት ኢትዮጵያ እንደ “አረንጓዴ አሻራ” ያሉ ሀገር በቀል ፕሮጀክቶችን እና ታዳሽ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ተሞክሮዎቿን እንደ ዋና ማሳያ ታቀርባለች።
ታዳጊ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎችን ለመቋቋም በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እና የደን ልማት ምን ያህል ወሳኝ እንደሆኑ ኢትዮጵያ ለማሳየት የምትሄድበት ተሞክሮ ትልቅ ማረጋገጫ ይሆናል። ይህም አገሪቱ በአለም አቀፍ ደረጃ በአረንጓዴ አሻራ ፋይናንስ ተጠቃሚ እንድትሆን የሚያስችላትን እድል ያሰፋላታል።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በ COP 32 የምታደርገው ዝግጅት የታዳጊ ሀገራትን ድምፅ በግንባር ቀደምትነት ለማሰማት ትልቅ መድረክ ይሆናል። ኢትዮጵያ ጉባኤውን ስታካሂድ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ የራሷን ዘላቂ ጥቅም ከማረጋገጧም በላይ፣ ለአፍሪካ ሀገራት የአየር ንብረት ጥያቄዎች ጠንካራ መሟገቻ መድረክ በመሆን ታሪካዊ አሻራዋን ታሳርፋለች።
በ- ታደለ ገበየሁ












