የአደባባይ ፕላዛዎች በጥንታዊ ግሪክ እና በሮም ተጀምረው በዓለም አቀፍ ደረጃ የአሜሪካው ታይምስ ስኩዌር እና የሩሲያው ቀይ አደባባይ ሰፊ እውቅና አላቸው።

በእኛም ሃገር ለረጅም ዘመናት የአደባባይ ፕላዛዎች ለሃይማኖታዊ፣ ለፖለቲካዊ እና ለህዝባዊ ስብሰባዎች በዋናነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
በ2012 ዓ.ም እድሳት የተደረገለት መስቀል አደባባይ የከተማዋን እድገት፣ የታሪክ ሂደት እና የማህበራዊ ትስስር ለውጦችን በጉልህ የሚያሳይ ዋና መዘክር ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
በአዲስ አበባ ከተማ በተጠናቀቁት ዋና ዋና የኮሪደር ልማት መስመሮች ከ30 በላይ ታዋቂና መጠነ-ሰፊ የህዝብ መዝናኛ ፕላዛዎች ተገንብተው ለህዝብ አገልግሎት በቅተዋል።
በካሳንቺስ ኮሪደር 16 የህዝብ ፕላዛዎች የተገነቡ ሲሆን፤ እንደ አድዋ ድል መታሰቢያ ፕላዛ ያሉ ታላላቅ የህዝብ መዝናኛ ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ።
አዳዲሶቹ ፕላዛዎች በመሬት ውስጥ ከ1,400 በላይ መኪናዎችን በአንድ ጊዜ ማቆም የሚችሉ ሰፊ ዘመናዊ ማቆሚያዎችን እና የስፖርት ማዘወተሪያ ትራኮችን አካተው ይዘዋል።

በተጨማሪም ለአካል ጉዳተኞች፣ ለህጻናት እና ለእግረኞች ምቹ የሆኑ መንገዶችን፣ ግዙፍ የዲጂታል ማስታወቂያ ሰሌዳዎችን እና ሰው ሰራሽ የውሃ ምንጮችን በመያዝ ለበርካታ ሰዎች አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።
እነዚህ ፕላዛዎች ነዋሪዎችና ጎብኚዎች በነጻነት የሚዝናኑባቸው፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚያደርጉባቸው እና ማህበራዊ ትስስርን የሚፈጥሩባቸው ምቹ ስፍራዎች ናቸው።
ከዚህም በላይ ሙዚቀኞች፣ ሰዓልያን እና የተለያዩ የኪነ-ጥበብ ባለሞያዎች ክህሎታቸውን የሚያቀርቡባቸው ክፍት መድረኮች ሆነው በማገልገል ለባለሞያዎች መንገድ በመክፈት ጎላ ያለ ሚና ሲጫወቱ ለተመልካችም መዝናኛ ሆኗል። ከኮሪደር ልማቱ ጋር በተያያዘም ከ5200 በላይ የንግድ ሱቆችና ጊዜያዊ ባዛሮች የከተማዋን ኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን እያሳለጡ ይገኛሉ።
የአደባባይ ፕላዛዎች በከተማ ውስጥ ከመኪና ትራፊክ ነፃ ሆነው፥ ለማንኛውም ሰው ያለ ምንም ክፍያ ክፍት የሆኑ፥ መናፈሻ፣ ወንበር፣ ፏፏቴ እንዲሁም ማራኪ የመሠረተ-ልማቶች ያሏቸው አደባባዮች ናቸው:: አልፎም የሕዝብ የጋራ መገናኛ፣ መዝናኛና ማኅበራዊ ኹነቶች ማካሄጃ ክፍት ቦታዎችም ሆነው ያገለግላሉ::

እነዚህ ስፍራዎች፣ ሰዎች ከስራ ጫና ወጥተው አእመሯዊ እና አካላዊ እረፍት እንዲያገኙ የሚረዱ የአደባባይ መናፈሻዎች ናቸው።
በ – የአብሥራ ተፈራ












